የኢትዮጵያ የፍራፍሬ ምርት እመርታ- በአፍሪካ ሁለተኛዋ አቮካዶ ላኪ ሀገር

You are currently viewing የኢትዮጵያ የፍራፍሬ ምርት እመርታ- በአፍሪካ ሁለተኛዋ አቮካዶ ላኪ ሀገር

AMN- ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም

ባለፉት ዓመታት በዘላቂነት ሲተገበር የቆየው የ”አረንጓዴ አሻራ” መርሐ ግብር ሀገሪቱን በአረንጓዴ ለምለም ከመሸፈን ባለፈ ለምግብ ዋስትና እና ለውጭ ምንዛሬ ገቢ ያስገኘው ውጤት ፍሬያማ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛዋ ትልቋ የአቮካዶ ላኪ ሀገር መሆኗ የሀገሪቱን የግብርና እምቅ አቅም እና የኢኮኖሚ ትንሳኤ በግልጽ የሚያሳይ ታላቅ ምዕራፍ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከማሳደጉም ባለፈ ለምግብ ዋስትና እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ አጠቃላይ የአየር ንብረት ሁኔታዎችን አሻሽሏል። ይህም እንደ አቮካዶ ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች በበቂ እርጥበት እና በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

በለም መሬቶች ላይ የተከናወነው የችግኝ ተከላ እና የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች አፈሩን ጠብቆ ለማቆየት ያስቻሉ ሲሆን፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት በስፋት እንዲስፋፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ለም መሬቶች እና ተስማሚ አግሮ-ኢኮሎጂካል ዞኖች ያሏት በመሆኗ ለፍራፍሬዎች ምርት ተስማሚ ናት።

የኢትዮጵያ አቮካዶ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ገበያዎች ከፍተኛ ጥራት ያለው በመሆኑ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።

ዘመናዊ የማሸጊያ እና የጥራት ቁጥጥር ማዕከላት መዘርጋታቸው ምርቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበትን አቅም አጠናክሮታል።

ሀገሪቱ በአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መድረሷ የሚያበረታታ ቢሆንም፣ይህ አሠራር ተጠናክሮ ከቀጠለ አንደኛ ደረጃን መያዝ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በዘንድሮ የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ወቅት አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አቮካዶ ኤክስፖርት ማደግ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎች ሕያው ማሳያ ነው።

መርሃ ግብሩ የዜጎችን ሕይወት የሚቀይር፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ የግብርና ትንሳኤ ግንባር ቀደም አድርጎ ያስቀመጠ ታላቅ ብሔራዊ ምዕራፍ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review