AMN- ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመዲናዋ ያስጀመራቸው ሁለንተናዊ የበጎ ፈቃድና የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ፣ የትብብርና የመረዳዳት ባህልን እያጎለበቱ ይገኛሉ።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከ55.7 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ማኅበረሰቡ እንዲረዳዳ ማድረግ ተችሏል።

በዚህም ማኅበረሰቡ የራሱን ችግር በራሱ አቅም መፍታት እንዲችል ማስቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማኅበረሰብ ተሳትፎ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ አስራት ንጉሴ ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ጠንካራ ማኅበረሰብና ትውልድ እየገነባ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በክረምትና በበጋ ወራት በሁለት ምዕራፎች በተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የዘመሙ ጎጆዎችን በመጠገን ለኑሮ ምቹ የሆኑ ቤቶችና የበጎነት መንደሮች ተገንብተዋል።

በተጨማሪም የነፃ ሕክምና፣ የደም ልገሳ እና የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብሮች በትኩረት በመከናወናቸው በበርካታ ዜጎች ላይ የነበረው የኑሮ ጫና ሊቃለል የቻለ ሲሆን፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ አብሮነት ከፍ እንዲል አድርጓል።
ኮሚሽኑ ለዘንድሮው ክረምት 18 የስምሪት መስኮችን በመለየት ከሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም ድረስ የሚከናወን ዕቅድ ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል።

በዚህም መሠረት 9.8 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ፣ 3.3 ሚሊዮን የሚጠጉ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እና 2.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማሳተፍ ሰፊ ግቦች ተይዘው ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

መረዳዳትና መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ባህልና የሁሉም እምነቶች መሠረታዊ አስተምሮት መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን መልካም እሴት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ምክትል ኮሚሽነሯ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው