መንግሥት ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል

You are currently viewing መንግሥት ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን ለማስወገድ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል

AMN – ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም

የመደመር አስተሳሰብን መርህ አድርጎ ሀገርን እየመራ ያለው መንግሥት የሀገርን ሀብት ለጥቂቶች ብልጽግና የሚያውሉ የሌብነትና የብልሹ አሠራር ድርጊቶችን በፍጹም እንደማይታገሥና ሌብነትን ከስሩ ነቅሎ ለማስወገድ ዘመነኛና ሰፊ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጿል።

መንግሥት የሕዝብን ጥያቄና እምነት ለማስጠበቅ ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር እና ግልጽነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት ከሕግ ተጠያቂነት ጀምሮ በበርካታ ዘርፎች የጀመራቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ ቀጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማንኛውም ሥልጣንና ኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኝ አካል ከሕግ በላይ ሊሆን እንደማይችል በማስመር፣ በሙስናና በብልሹ አሠራር የተጠረጠሩ አካላትን ያለአንዳች አድልዎ ለሕግ የማቅረብና ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ማንሳታቸው ይታወሳል።

ሌብነትንና ሙስናን በስርዓት ለመታገል የሚያስችሉ ልዩ ብሔራዊ ኮሚሽኖችንና የሕግ ማዕቀፎችን በማጠናከር፣ የመንግሥት አሠራር ከግል ጥቅም ይልቅ ለሕዝብ አገልግሎት ብቻ እንዲውል የሚያስገድዱ አሠራሮች መዘርጋታቸውንም ተናግረዋል።

የተገልጋዮችና የአገልግሎት ሰጪዎች ቀጥታ ንክኪን የሚቀንሱ የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት በመተግበር፣ አገልግሎቶች ግልጽ፣ ቀልጣፋና ለብልሹ አሠራር በር የማይከፍቱ እንዲሆኑ መደረጉንም ነው ያመላከቱት።

የመንግሥት ሀብትና ንብረት ብክነትን ለመግታት የኦዲትና የፋይናንስ ቁጥጥር ሥርዓቶች ተጠናክረዋል፤ ባልተገባ መንገድ የተገኘ ንብረትና ሀብት ለሕዝብና ለሀገር ገቢ የሚሆንበት የሕግ መሥመር ተዘርግቶም እየተተገበረ ይገኛል።

ኅብረተሰቡ የሌብነትና የብልሹ አሠራር ተፃራሪ እንዲሆን ጥቆማዎችን የሚሰጡበትና ጠቋሚዎች ጥበቃ የሚደረግላቸውን ሥርዓቶች በማስፋት የሕዝብ ቁጥጥርና አጋርነት እንዲጎለብት ተደርጓል።

የመደመር መንግሥት የጀመረውን የሪፎርም ጉዞ ለማስቀጠል፣ ሀገራዊ እድገትንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን እስከመጨረሻው የመታገል ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review