መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህገ-ወጥነትንና ብልሹ አሰራርን በማስቀረት የህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ ነው

AMN- ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህገ-ወጥነትንና ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ጥራት ያለው አገልግሎት ለህዝብ ተዳራሽ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት አሰራርን ለማዘመን ከጀመራቸው ስራዎች መካከል የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ይጠቀሳል።

ማዕከሉ ብልሹ አሰራርን፣ ህገ-ወጥነትንና ሌብነትን በዘላቂነት ለማስቀረት ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል። አገልግሎቱ ዜጎች ያለ እንግልት እና የደላላ ጣልቃ ገብነት ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ አስችሏል።

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በከተማዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተስፋፍቷል፡፡ በከተማዋ በተንቀሳቃሽ አውቶብስ የሚሰጥ የዲጂታል አገልግሎትም ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ይህም አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን በማስቀረት እና አሰራርን ግልጽ በማድረግ የፀረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ አድርጎታል።

በከተማ ደረጃ የተጀመሩ የኦዲት እና የቁጥጥር ሥርዓቶች እንደሚያሳዩት ተቋማዊ አሰራርን በቴክኖሎጂ መደገፍ የተገልጋዮችን ድካም በመቀነስ የሙስና ስጋትን በከፍተኛ ደረጃ ይቀርፋል። ይህም ህብረተሰቡ በፍጥነት የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ያደርጋል።

በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ውጤቶች እንደሚያመላክቱት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት አሰራሩን ማዘመኑ የፋይናንስ ስርዓቱን በጥብቅ ለመቆጣጠር ያስቻለ ሲሆን የሚሰጡ አገልግሎቶችም ፍትሃዊ፣ ፈጣን እና ግልጽ እንዲሆኑ አድርጓል።

በአጠቃላይ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስፋፋት ህገ-ወጥነትን በመከላከል፣ የከተማዋን ኢኮኖሚ ከብክነት በመጠበቅ እና የህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ ነው።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review