AMN- ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙትን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን ኦባይድ ሀሰን አል-ሻምሲን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ሃደራ፣ ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን የረዥም ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያነሱ ሲሆን፣ በተለይም በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የህዝብ-ለህዝብ አጋርነቷን አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት ገልፀዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ያነሱት አምባሳደሩ፣ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ሴክተሮች በግብርናው ዘርፍ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይሲቲ፣ በቱሪዝም፣ በፋይናንስ፣ በኢነርጂና በሎጀስቲክስ ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ተሿሚው አምባሳደር አብደላ በበኩላቸው፣ የብሔራዊ ምክክር ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በማስመልከት ለኢትዮጵያ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልም ምስጋናቸውን ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በጋራ ፍላጎቶች እና በቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ሃሳብ የተለዋወጡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት ይበልጥ ለማስቀጠል አብሮ ለመሥራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።