AMN-ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተሟላና ዘመናዊ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ይበልጥ አትራፊ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ በስሩ የሚገኙ ሰባት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የ2018 እቅድ አፈጻጸም እና የ2019 ዕቅድ የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
የመንግስት ልማት ድርጅቶችን ይበልጥ ውጤታማ፣ አትራፊ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተንኩዌይ ጆክ ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በተደረገው ጠንካራ ድጋፍና ክትትል ኪሳራ ውስጥ የነበሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ከኪሳራ በማውጣት ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ532 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግስት ፈሰስ መደረጉን አቶ ተንኩዌይ ጆክ ተናግረዋል። ይህም ለከተማዋ ኢኮኖሚ የገቢና የሀብት አቅም ማሳደግ ስለመቻሉ አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የተገኙትን ውጤቶች በማላቅ በ2019 በጀት ዓመት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተመላክቷል።
በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የልማት ድርጅቶች እውቅና እና የሽልማትም ተበርክቶላቸዋል።
በመሀመድኑር አሊ