የአዲስ አበባን ውበት ለማስጠበቅና የደንብ መተላለፎችን ለመከላከል የህብረተሰቡ ሚና የላቀ ነው

AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን “የተቋሙን ስኬቶች ለማስቀጠል የህብረተሰቡ ድርሻ የላቀ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ከተማ አቀፍ የህዝብ ውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት፤ ባሳለፍነው በጀት ዓመት የተመዘገቡት የደንብ ማስከበር ስኬቶች የህብረተሰቡና የባለድርሻ አካላት አጋርነት ውጤት ናቸው ብለዋል።

አክለውም በቀጣይ በስነ-ምግባር የታነፀ ባለሙያ በመገንባት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታትና ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የደንብ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በውይይቱ የባለስልጣኑ የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ለነዋሪዎች የቀረበ ሲሆን፣ ተቋሙ በቀጣይ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎችን ለመፍታትና የደንብ መተላለፎችን ለመቀነስ እንደሚሰራ ተመላክቷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአካባቢያቸውን ሰላምና ደንብ ለማስጠበቅ ከተቋሙ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የገለጹ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳቦችና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት መድረኩ መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review