ኤጀንሲው የመሬት ምዝገባ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ መሶብ የዲጂታል አገልግሎት ለማሸጋገር እንደሚሰራ አስታወቀ

AMN – ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የመሬት ምዝገባ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ መሶብ የዲጂታል መስኮት አገልግሎት ለማሸጋገር እንደሚሰራ አስታውቋል።

ተቋሙ ቀደም ሲል በከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የብልሹ አሰራር ስጋት አለባቸው ከተባሉ 16 ተቋማት አንዱ የነበረ ቢሆንም፣ ባካሄደው የጥልቅ ሪፎርም፣ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማሻሻያ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ በአረንጓዴ ደረጃ ተመድቧል።

ኤጀንሲው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀሙን እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅዱን ከባለድርሻ አካላት ጋር የገመገመ ሲሆን፣ ባሳለፍነው በጀት ዓመት በተለይም የክርክር መዝገቦችን በማቃለል፣ በግንዛቤ ፈጠራ፣ የይዞታ ማረጋገጥ፣ በመረጃ ጥራት እና በገቢ አሰባሰብ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ገልጸዋል።

ኤጅንሲው 14.49 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 14.64 ቢሊዮን ብር በማስገባት 101 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተገልጿል።

98 ሺህ የክርክር መዝገቦችን ማቃለል የቻለ ሲሆን ፣ ለስጋት ተጋላጭ የነበሩ ከ58 ሺህ በላይ መዝገቦችን በኦዲት በማጣራት እና በማስተካከል የመረጃ ጥራቱን ማረጋገጡ ተጠቅሷል።

1 ሺህ ሳይቶችን እንዲሁም 33 ሺህ 717 የጋራ መኖሪያና የሪል ስቴት ቤቶችን በማረጋገጥ ለህጋዊ ምዝገባ ማሸጋገሩ ነው የተገለፀው።

በተጨማሪም 36 ሺህ 500 ባለ ይዞታዎች ጋር በአካል በመድረስ 102.5 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገቡ ተመላክቷል።

ኤጀንሲው ለዚህ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና የሰጠ ሲሆን፣ የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በዜና፣ በምርመራ ዘገባዎቹ እንዲሁም በዋርካ፣ በጠረጴዛ እና በአገልጋይ ፕሮግራሞቹ አገልግሎቶችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ እና ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና ተበርክቶለታል።

ተቋሙ በቀጣይም የመሬት ምዝገባ አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ መሶብ የዲጂታል መስኮት በማሸጋገር ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን በዘላቂነት ለማስወገድ እንደሚሰራ አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review