AMN- ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕፃናት በተገቢው እንክብካቤ አድገው የነገ ተስፋቸው እንዲሰምር ለማስቻል የጀመረው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
በከተማ አስተዳደሩ በ2015 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮግራም መዲናዋን ለሕፃናት እድገት ምቹ የሆነች የአፍሪካ ከተማ የማድረግ ራዕይ ሰንቋል።
ፕሮግራሙ ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ባሉ ሕፃናት ላይ በማተኮር አጠቃላይ ጤንነትን ማረጋገጥ፣ አልሚ ምግብ ማቅረብ፣ እንክብካቤ መስጠት፣ የመማር ዕድል ማመቻቸት እና አስፈላጊውን ጥበቃና ደህንነት ማቅረብን ያካትታል።
በቅድሚያ በድህነት ውስጥ የሚኖሩና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ወላጆችና ሕፃናት መደገፍ ላይ ያተኮረ ቢሆንም በሂደት የከተማዋን ወላጆችና ሕፃናት የሚያቅፍ ተቋማዊ አሰራር ዘርግቷል።
መዲናዋን መነሻ ያደረገው ይህ በጎ ጅምር በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም እየተስፋፋ ይገኛል።
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ የሚያካሂደው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም እና በየአካባቢው የተገነቡት የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች የሕፃናትን ስነ-ልቦናዊና አካላዊ ዕድገት በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው።
በዚህም የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ላይ በተሰራው ሥራ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፉ ‘Act For Early Years’ ኢኒሼቲቭ ዘንድ የ“ቅድመ ልጅነት እድገት ሻምፒዮን” ተብለው እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ይህም አዲስ አበባን በአፍሪካ የቀዳማይ ልጅነት እድገት የከተማ አመራር ተምሳሌት አድርጓታል።
በትዝታ መንግስቱ