ጳጉሜን – የዕድሳት፣ የይቅርታ እና የአስራ ሦስተኛው ወር ድምቀት

You are currently viewing ጳጉሜን – የዕድሳት፣ የይቅርታ እና የአስራ ሦስተኛው ወር ድምቀት

AMN – ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም

የሰው ልጅ ከቀደመው ዘመን ጀምሮ መኖሪያው ካደረጋቸው ስፍራዎች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከቀን መቁጠሪያ ባለፈ የራሷ የሆነ የዘመን ቀመር አላት።

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከፈረንጆቹ ግሪጎሪያን አቆጣጠር ሰባት እስከ ስምንት ዓመታት የሚዘገይ ነው።

ምንም እንኳ ግሪጎሪያን አቆጣጠር ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ቢኖረውም፣ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ስሌት መሠረት የምድርን ዙሪያ ከፀሐይ አንጻር በማስላት ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ አቆጣጠር ነው።

ይህ ልዩ አቆጣጠር ከአስራ ሁለቱ መደበኛ ወራት በተጨማሪ የራሷ ድምቀት ያላት ጳጉሜንን ያካትታል።

ከመስከረም እስከ ነሐሴ ያሉት አስራ ሁለቱ ወራት እያንዳንዳቸው 30 ቀናት ሲኖራቸው፤ ጳጉሜን ከእነዚህ መደበኛ ወራት ውጭ የምትገኝ፣ የዓመቱ የመጨረሻ ቀናት እና ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የምታሸጋግር የሽግግር ወቅት ናት።

“ተጨማሪ ቀናት” ወይም “ተደራቢ” የሚል ትርጉም ያላት ይህች ወር በየአራት ዓመቱ የሚቀያየር አቆጣጠር ያላት ሲሆን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ 5 ቀናት ሲኖሩት፤ በዘመነ ዮሐንስ መጀመሪያ ላይ ግን 6 ቀናት ሆና ትቆጠራለች።

ጳጉሜን በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አስራ ሦስተኛዋ ወር ስትሆን፣ ፣ በአሮጌው እና በአዲሱ ዓመት መካከል የምትገኝ የሽግግር፣ የዕድሳት፣ የይቅርታ እና የተስፋ ወቅት ናት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት ደረጃ የጳጉሜን ቀናቶች በተለያዩ መሪ ሀሳቦች ታስበው መዋል መጀመራቸው ቀኑን ይበልጥ ትርጉም ያለው አድርጎታል።

የዘንድሮው የጳጉሜን ቀናቶች እንደየቅደም ተከተላቸው የእመርታ ቀን፣ የማንሰራራት ቀን፣ የጽናት ቀን፣ የኅብር ቀን እና የነገ ቀን በመባል ከነገ ጀምሮ ይታሰባሉ።

ይህ ልዩ የዘመን አቆጣጠርና የጳጉሜን ማሳረጊያ ሥነ-ሥርዓት ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን የሚስብ ትልቅ ሐብት ነው።

ይህም ኢትዮጵያ የአስራ ሶስት ወር ፀጋ ባለቤት መሆኗንና ዓለምን በልዩነቷና በባህሏ እንደምትማርክ በግልጽ ያሳያል።

በበረከት ጌታቸው

S

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review