AMN- ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአከራይ እና ተከራይ የውል እድሳት አፈጻጸም እስከ ጳጉሜን 5 ቀን ድረስ መራዘሙን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የቤት ጥናት እና መረጃ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተዋቡ ቀስቅስ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ታቅዶ የነበረው የውል እድሳት ሂደት ለ30 ተጨማሪ ቀናት ተራዝሞ ስራው ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለውም፣ ከተጠበቀው አጠቃላይ ተከራይና አከራይ ህዝብ ውስጥ እስካሁን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ውላቸውን ማደሳቸውን ገልጸው፣ ይሁን እንጂ በየማዕከላቱ የታየውን መጨናነቅ፣ ከከተማ ውጭ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጥያቄ እና አጠቃላይ ያለውን ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎቱ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል ብለዋል።
አገልግሎቱ በየማዕከላቱ እንዲሁም በ”መሶብ” ማዕከል ከጥዋት እስከ ምሽት ድረስ እየተሰጠ እንደሚገኝ የጠቆሙት ምክትል ሃላፊዋ፣ አከራዮችና ተከራዮች እስከተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ ድረስ በአካል በመቅረብ ውላቸውን እንዲያድሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ውላቸውን የማያድሱ አካላት ወደ ቅጣት አሰራር የሚገቡ በመሆኑ፣ አከራይና ተከራይ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ በመያዝ በጋራ ቀርበው ውላቸውን ማደስ እንዳለባቸው የቢሮው የቤት ጥናት እና መረጃ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ተዋቡ ቀስቅስ አሳስበዋለ።
በአስማረ መኮንን