AMN- ጳጉሜን 2/2018 ዓ.ም
ዓለም ለዘመናት የኢትዮጵያን ስም ሲያነሳ ከረሃብና ከችግር ትርክት ጋር አያይዞ መሳል ይቀለዋል፡፡ አዲስ አበባ ይህን የቆየ ስዕል በሥራ እየቀየረች የአዲስ ዘመን “ማንሰራራት” ሕያው ምስክር ሆናለች፡፡
የነገዋ ኢትዮጵያን ተረካቢ ትውልድ በጠንካራ መሰረት ላይ እያነጸች ያለችው አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አማካኝነት የአፍሪካ አልፎም ለዓለም ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በ2015 ዓ.ም የተጀመረው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አዲስ አበባን ለሕጻናት እድገት ምቹ የሆነች የአፍሪካ ከተማ የማድረግ ራዕይን የሰነቀ ነው ፡፡
ፕሮግራሙ ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ባሉ ሕጻናት ላይ በማተኮር አጠቃላይ ጤንነትን ማረጋገጥ፣ አልሚ ምግብ ማቅረብ፣ እንክብካቤ መስጠት፣ የመማር ዕድል ማመቻቸት እና አስፈላጊውን ጥበቃና ደህንነት ማቅረብን አካቶ ይዟል፡፡
ፕሮግራሙ 330 ሺህ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦችን ጨምሮ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሕጻናትን ታሳቢ በማድረግ እየተተገበረ ሲሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ከ50 በመቶ በታች የነበረው የሕጻናት የመደበኛ ትምህርት ዝግጁነት ከ99 በመቶ በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

5 ሺህ ባለሙያዎች በየ15 ቀኑ የቤት ለቤት የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ለ15 ሺህ እናቶችና ሕጻናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እንዲሁም በ95 ጤና ጣቢያዎች በተደረገ ከ817 ሺህ በላይ የዕድገት ክትትል፣ የሕጻናት መቀንጨር ወይንም የዕድገት ውስንነት በ 4 በመቶ መሻሻል በማሳየት ከ13 ወደ 9.45 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
በተጨማሪም ለህጻናት እድገት እና ጤንንት ምቹ ለማድረግም 1 ሺህ 155 የሕጻናት ማቆያዎች እና ከ5 ሺህ በላይ የመጫወቻ ቦታዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡
አዲስ አበባ የሕጻናቷ ተስፋ ከማለምለም አልፋ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት መሳብ ችላለች፡፡
ከተማዋ በዘርፉ ያስመዘገበችውን አመርቂ ውጤት ተከትሎም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፉ ‘Act For Early Years’ ኢኒሼቲቭ የ“ቅድመ ልጅነት እድገት ሻምፒዮን” ተብለው ከፍተኛ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ዓለም አቀፉ የቀዳማይ ልጅነት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ከተማዋ ያላትን ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት እንድታካፍልና የአፍሪካ ተምሳሌት መሆኗን ያረጋገጠ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ እጥረትና በረሃብ ትገለጻለች የሚለውን የቆየ ትርክት፤ አዲስ አበባ ሕጻናትን በመመገብ፣ በማስተማር፣ የጤና ክትትል በማድረግና ምቹ የመጫወቻ ስፍራዎችን በመገንባት በተግባር እያንሰራራች ትገኛለች፡፡
በትዝታ መንግሥቱ