AMN- ጳጉሜን 05/ 2018 ዓ.ም

መዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአስተሳሰብ፣ በመሠረተ ልማት፣ በጽዳትና በአረንጓዴ ልማት እንዲሁም በማህበራዊ አገልግሎቶች ታይቶ የማይታወቅ ሁለገብ ለውጥ በማስመዝገብ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ውብ መሆኗን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2019 ዓ.ም አዲስ አመትን አስመልክቶ ስለ አዲስ አበባ ለውጥና አሁን ስለ ሚታየዉ ከፍታ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ እና ነዋሪዎችን ተጠቃ ያደረጉ አበይት ስኬቶች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ከንቲባ አዳነች በማብራሪያቸው ከተሰሩትና ለውጥ ከመጣባቸው ስራዎች መካከል ትናንት ሲያከራክሩ እና ሲያጋጩ የነበሩ የተበታተኑ ትርክቶች ቀርተው፣ የሁሉንም ህብረተሰብ አንድነት የሚያጠናክሩ አሰባሳቢ ትርክቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
ከንቲባ አዳነች አክለውም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል የሆነውን የአድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ ትውልዱ የጋራ ድሉን በጋራ እንዲዘክር ትልቅ መሠረት መጣሉን አንስተዋል።
ጽዳት የጤንነት ጉዳይ መሆኑ ታምኖበት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ ከሰባት ዓመት በፊት 2.8 በመቶ ብቻ የነበረው የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋን ዛሬ ላይ 24 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ዝቅተኛ መተዳደሪያ ባለባቸው እና ያረጁ ጭቃ ቤቶች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ፣ አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶችና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች በመገንባታቸው የነዋሪዎች ክብር ያለው ሕይወት እንዲኖሩ ማስቻሉን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
የመንገድ ሽፋን ከ12.8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማደጉን፣ የመኪና ማቆሚያ አቅም ከነበረበት 3ሺ አድጎ ዛሬ 180ሺ መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም ወደ ሚያስችል ደረጃ መድረሱን እና የውሃ አቅርቦት በ60 በመቶ መጨመሩን ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡
ለውጡ በፊት 1 ብቻ የነበረው ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ፋብሪካ ዛሬ 47 መድረሱ የከተማዋን ንጽህና ለመጠበቅ ትልቅ እመርታ ሆኗል ብለዋል ።
ተማሪዎች እየተመገቡ እንዲማሩ በመደረጉ የወላጆች ጫና መቀነሱን፣ የጤና ተቋማት በመስፋፋታቸው ከተማዋ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ፣ እንዲሁም በኮንስትራክሽንና አገልግሎት ዘርፎች ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ እድል ማግኘታቸውም አብራርተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባ ወደ እውነተኛ የቱሪስት መዳረሻነት መሸጋገሯን ጠቅሰው፤ ይህም አፍሪካውያን መስራት ይችላሉ የሚለውን አዎንታዊ አስተሳሰብ በሰው አእምሮ ውስጥ መቅረጽ የቻለ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን በአጽንኦት አስረድተዋል።
በአስማረ መኮንን