AMN- መስከረም 03/2019 ዓ.ም

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቪላዲሚር ፑቲን አፍሪካ፣ እስያ እና ላቲን አሜሪካ የተሻለ ውክልና እንዲያገኙ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት እንዲሰፋ ጥሪ አቀረቡ።
በኒው ደልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ፑቲን፣ ምክር ቤቱን ማሻሻል የተመድ ተልዕኮ ውጤታማነት ከፍ እንዲል እና የዛሬውን ዓለም አቀፍ የሃይል ሚዛን በተሻለ ሁኔታ ማንጸባረቅ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
አፍሪካ ከተመድ አባል አገራት ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆኑትን ብትይዝም፣ በጸጥታ ምክር ቤቱ ውስጥ ግን ምንም ዓይነት ቋሚ መቀመጫ የላትም።
የአፍሪካ ህብረት የተሻለ ውክልና እንዲኖረው ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ ቆይቷል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ፑቲን የአሁኑን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ እውነታዎች በተሻለ ሁኔታ ማንጸባረቅ እንደሚገባቸው በመጥቀስ የዓለም የገንዘብ ፈንድ፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም የንግድ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ዘገቧል፡፡
በአስማረ መኮንን