AMN – መስከረም 09/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መዲና እና የበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ፣ በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ ሁለገብ የልማትና የንጽህና ስራዎች አማካኝነት ገጽታዋ እየተቀየረ ይገኛል።
በከተማዋ የተከናወኑ ግዙፍ የኮሪደር ልማቶች እና በሕዝባዊ የጽዳት ንቅናቄዎች የተከናወኑ የጽዳት ስራዎች አዲስ አበባ ከነበረችበት የጽዳት ችግር ተላቃ በዓለም መድረክ አዳዲስ ገጽታዎችን እንድትጎናፀፍ አስችሏታል፡፡
በአንድ በኩል በጂኦስፔሻል አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋማት ጥናት መሰረት ከፍተኛውን የአየር ንብረት ጽናት በማስመዝገብ ከዓለም ሁለተኛ መሆኗ ሲነገር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ጥልቅ የጽዳትና የውበት ስራዎች መዲናዋን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭና ንጹህ ከተማ እንደሆነች አድርገዋታል፡፡
እነዚህ የከተማዋን ውበት እና ጽዳት ወደ ተሻለ ከፍታ ለማውጣት የተደረጉት ርብርቦች ለአዲስ አበባ ከተማ ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ጋር የሚጣጣሙ ትላልቅ ስኬቶችን አስመዝግበዋል።
ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በታሪኳ አዲስ በሆኑ ዘመናዊ የኮሪደር ልማቶች፣ በሰፋፊ ጐዳናዎች፣ በሕዝብ ማረፊያና ማሻሻያ ቦታዎች እንዲሁም ማራኪ መናፈሻዎች መታጀቧ፣ አዲስ አበባን በአፍሪካ ደረጃ ተመራጭና ውብ ከፍታ ላይ እያስቀመጧት ይገኛሉ።
ይህ እውነታ ከተማዋ ከምታከናውናቸው አረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ የሚከናወነው ዓለም አቀፍ የጽዳት ቀን ንቅናቄ “ከንፁህ ሳህኖች ወደ ንፁህ ከተሞች!” በሚል መሪ-ሀሳብ በመዲናችን አዲስ አበባ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጽዳትን እንደ አንድ የባህል መገለጫ እና የዕለት ተዕለት ልማድ አድርጎ ለማስረጽ የታለመው ከተማ አቀፍ ንቅናቄ፣ የከተማ ግሪን ሌጋሲ እና የውበት ስራዎች ከዓለም አቀፍ ዘላቂ የልማት ግቦች ጋር አብረው እንዲጓዙ እያደረገ ይገኛል።
በአጠቃላይ፣ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች እና የጽዳት ስራዎች መዲናዋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ተመራጭ፣ ለኑሮ ምቹ እና ንጹህ ዓለም አቀፍ ከተማ እያደረጓት ይገኛሉ።
ይህ የለውጥ ጉዞ አዲስ አበባን በአህጉሪቱና በዓለም መድረክ የላቀ ተሰሚነት እና ስም እንዲኖራት አድርጓታል።
በአስማረ መኮንን