AMN- ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት እስከ አሁን ያለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅና ተስፋ ሰጪ ለውጦች የሚታዩበት መሆኑ ተገለጸ፡፡
ከ ኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ሰለሞን ተፈራ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ረጅም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ያላት ሀገር እንደ መሆኗን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በመንግሥትና በመንግሥት፣ በመንግሥትና በሕዝብ እንዲሁም በሕዝብና በሕዝብ መካከል የተለያዩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጥያቄዎችና የሀሳብ ልዩነቶች አንደነበሩ ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እነዚህን ልዩነቶች በመቅረፍ ተቀባይነት ያለው የሀገር ግንባታ ሂደት እውን ለማድረግ ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

የብሔራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ የዛሬውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ልዩነቶች መነሻዎች በጥልቀት ማጥናትና ቁልፍ ሐሳቦችን ማቅረብ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የመንግሥት አወቃቀር፣ የፖለቲካ ድርጅቶች አሠራር ወይም የፖለቲካ ማዕቀፎች የመሰሉ ማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመመርመር ለችግሮቹ ተስማሚ የሆኑ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥንም እንደሚያካትት አንስተዋል።
በምክክር ሂደቱ ውስጥ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ አለመኖሩን መረዳት ያስፈልጋል ያሉት መምህር ሰለሞን፣ በዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንደሚታየው ብሔራዊ ምክክር ሦስት ዐበይት ውጤቶችን ሊያስገኝ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ይህም የተሻለ መግባባት ላይ መድረስ፣ መቻቻልን መፍጠር እና መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ነጥቦች ካሉም መዝግቦ ለቀጣይ ምክክር ማስተላለፍ የሚሉት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ዕርቅ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በሂደት የሚዳብር በመሆኑ፣ ጅምር ሂደቱ እጅግ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
የምክክሩን ሂደት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አንጻር ሲታይ፣ የአጀንዳዎችን ስፋትና ጥልቀት፣ የሕዝብ ብዛት እና የማኅበረሰቡን ሥነ-ልቦናዊ ግንባታ ማጤን ተገቢ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት 130 ሚሊየን ሕዝብ ብዛት እና ከሰፊና ውስብስብ የብሔር ስብጥር አንፃር፣ የምክክር ሂደቱ አሁን የደረሰበት ደረጃ እና ያስመዘገበው ስኬት እጅግ አበረታችና በቀላሉ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ