AMN- መስከረም 16/2019 ዓ.ም
የሀገራችን ድምቀትና የዓለም ቅርስ ከሆኑ የአደባባይ በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል በሁሉም ባለድርሻዎች ትብብር በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ በከፍተኛ ድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
በ2019 የመስቀል ደመራ በዓል ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የከተማችን ድምቀት ከሆኑ የአደባባይ በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል ለዘመናት ሐይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በባህላችን ደምቆ ሲከበር የኖረ ታላቅ በዓል ነው ብለዋል፡፡
የመስቀል በዓል መሠረት በይቅርታና በፍቅር የመሻገር መሆኑን ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በዓሉን ስናከብር በፍቅርና ይቅርታ በዓሉ ያለውን ተምሳሌትነት እያሰብን፤ እርስ በእርስ በመዋደድ እና በመከባበር እንንዲሁም በመደጋገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ሲከበር በርካታ ዘመን ተሻጋሪ ሁለንተናዊ ፋይዳዎችን አ ቅፎ ይዛል ያሉት ከንቲባዋ፤ በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ በይፋ ተመዝግቦ የሰው ልጅ የጋራ ማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ በመሆን በዓለም ሀገራዊ ገፅታችንንና የባህል ሃብታችንን ከፍ ያደረገ እሴታችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በደመራው ዙሪያ የሚበሩት በርካታ ነጠላ ችቦዎች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ብርሃን ያላቸው፤ ነገር ግን ሁሉም በአንድነት ተሰብስበው ወደ ደመራው ሲቀላቀሉ አካባቢውን በሙሉ የሚያደምቅ፣ ጨለማውን የሚገፍና አቅጣጫን የሚያሳይ ታላቅ የጋራ ብርሃን ይፈጥራሉም ብለዋል፡፡ ይህም የእርስ-በርሳችን የተጋመደ አንድነታችን ከዚህ ተምሳሌት ጋር አንድነት እንዳለው ማሳያ ነው ማለታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

የተለያየ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ቢኖረንም እንደ ደመራው በጋራ ስንቆም፣እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንራመድና ህብረታችንን ስናጠናክር ለከተማችንና ለሀገራችን የማይበገር ታላቅ ብርሃንና ጥንካሬ እንሆናለን ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ደመራው የሚያስተላልፍልን ዋናው መልእክትም አብሮነት፣ህብረትና አንድነት ሁልጊዜም ጥንካሬ ፈጥሮ ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚሆን ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ከተማችን አዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የዓለም የስህበት ማዕከል፣የንፅህና ተምሳሌት፣ በአጭር ጊዜ የተከናወነ የከተማ ለውጥ አብነት ሆናለችም ብለዋል፡፡
በዚህች ውብ፣ ፅዱ እና ለመኖር ምቹ የሆነች ከተማችንን፣ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችንና ዓለማቀፍ እንግዶችን በታላ ስነ-ስርዓትና በብቃት እያስተናገደች ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
ከተማችን ታላላቅ ሀገር-አቀፍና ዓለም-አቀፍ ሁነቶችንና እንዲሁም ሀገራዊ የአደባባይ በዓላትን በስኬት የመምራት፣ የማስተናገድ አቅሟ በከ ፍተኛ ደረጃ ማደጉን ለዓለም እያስመሰከረች ነው ብለዋል፡፡
ለመላው የከተማዋና የሀገራችን ነዋሪዎችም መልካም የደመራ እና የመስቀል በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።