AMN – መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ትናንት በአዲስ አበባ እና በመላው ሀገሪቱ በድምቀት በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ የሀገር ውስጥ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ፣ አህጉር አቋርጠው የመጡ የውጭ ሀገር እንግዶች እና የዲያስፖራ አባላትም ታድመዋል።
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከናወነው የደመራ በዓል ላይ የተገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ስለ ኢትዮጵያ ባህል፣ ሕዝብ እና መስተንግዶ ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት በደስታ ገልጸዋል።

ከካሊፎርኒያ እና ከተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች የመጡ ወጣቶችና ታዳሚዎች፣ እንዲህ ዓይነት ግርማ ሞገስ ያለው እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚታይበትን በዓል አይተው እንደማያውቁ በአድናቆት ተናግረዋል።
በበዓሉ ላይ የሚቀርቡ ዝማሬዎች፣ የደመራው መብራት እና የክብረ በዓሉ መንፈሳዊ ትርጉም ለዓለም አቀፍ ክርስቲያኖችም ጭምር ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
ተሳታፊዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ ያገኙትን ሞቅ ያለ መስተንግዶ፣ የባህል ድምቀት እና የባህላዊ ምግቦች ጣዕም የማይረሳ ትዝታ እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ስለ በዓሉ ውበት፣ ስለ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ገጽታ እና ባህል ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው በኩራት እንደሚያጋሩ ገልጸው፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “መልካም የመስቀል በዓል” የሚል መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
በአስማረ መኮንን