የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱን አኩሪ ታሪኮች፣ ድሎች፣ ገድሎችና ማንነት የሚወክል ነው – ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

AMN-ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱን አኩሪ ታሪኮች፣ ድሎች፣ ገድሎችና ማንነት የሚወክል ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

19ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት ድምቀት ተከብሯል።

በአከባበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የአገሪቱን አኩሪ ታሪኮች፣ ድሎች፣ ገድሎችና ማንነት የሚወክል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር በአግባቡ ሲያስጠብቁ አገራቸውን ሲያሳድጉና ሲያበለጽጉ እንዲሁም ታሪካቸውን ሲያስቀጥሉ በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ያላቸው ኩራት የሚጎላ መሆኑንም አብራርተዋል።

አክለውም ሰንደቅ ዓላማን ከፍ አድርጎ ለማውለብለብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ እና አበርክቶ ከፍተኛ ሚና እንዳለው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የአገርን ሉአላዊነትና ሰንደቅ ዓላማን ለማስከበር በየድንበሩ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ጀግኖችን ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የስራ መስክ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review