AMN – ጥቅምት 7/2019 ዓ.ም

የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን በተሻለ ጥራት እና ፈጠራ ለመስራት እንዲነሳሱ በሚል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው “አደይ ኮንቴምፖራሪ አርት አዋርድ” በአድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።
አዲስ አበባ ለኪነጥበብ ስራዎች አመቺ ቦታዎችን ለመፍጠር በርካታ ስራዎችን እየሰራች በመሆኑ፣ አደይ ኮንቴምፖራሪ አርት አዋርድ “የኢትዮጵያ የፈጠራ ጥበባት አዲስ ገፅታ” በሚል መሪ ሀሳብ በየዓመቱ የኮንቴምፖራሪ አርቲስቶችን እውቅና ለመስጠት የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

አዋርዱ የክንውን ጥበባትን በኤግዚቢሽንና በመድረክ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲቀርቡ ለማስቻል፣ የጥበብ ባለሙያዎች እርስ በእርስ የሚደጋገፉበትን እና እየተፈጠረ ላለው ገበያ አርቲስቶች እራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትን እድል የሚፈጥር እንደሆነም ተጠቅሷል።
የሽልማት ሥነ ስርዓቱ በ6 ዘርፎች የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም በኮንቴምፖራሪ የዳንስ፣ የፋሽንና ሞዴሊንግ፣ የሰርከስ፣ የአጭር የቲከቶከ ፊልም፣ ስዕል እና በሙዚቃ ዘርፎች መሆኑ ተመላክቷል፡፡
መርሐ ግብሩን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሁሉም የሚዲያ አማራጮቹ በቀጥታ እያሰራጨ ይገኛል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ አፍቃሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
በታምራት ቢሻው