በአዲስ አበባ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ

You are currently viewing በአዲስ አበባ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ

AMN- ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ እንደገለጸው፤ አደጋዎቹ የተከሰቱት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13፣ ወረዳ 1 እና ወረዳ 15 ነው።

የመጀመሪያው አደጋ የደረሰው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 13 ልዩ ቦታው ጀሞ ቅዱስ ሚካኤል መብራት ከቀኑ 9፡30 አካባቢ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ምርመራ መምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መንግስቱ ታደሰ፤ የጉዞ አቅጣጫውን ከአየር ጤና ወደ ጀርመን አደባባይ ያደረገው ሲኖትራክ ተሽከርካሪ መብራት ይዟቸው ቆመው የነበሩ 10 ተሽከርካሪዎችን እና አንድ የመብራት ፖል ላይ በመግጨት የንብረት ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡

በአደጋውም በትራንስፖርት ተሽከርካሪ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ የ44 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አንዲት እናት ላይ የሞት፣ በአንድ ሌላ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም በ11 ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች የህክምና ርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ጀሞ ሦስት አካባቢ ፒክአፕ ተሽከርካሪ ይዞ ከጀሞ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ጀሞ ሶስት ሲጓዝ የነበረው አሽከርካሪ ከቀኝ ወደ ግራ ሲሻገር በነበረ ግለሰብ ላይ የሞት አደጋ ያደረሰ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

እንዲሁም በዚያው ክ/ከተማ ወረዳ 15 ሀጫሉ መንገድ አካባቢ ሀዩንዳይ ተሽከርካሪን በመያዝ ወደ ጋርመንት እያሽከረከረ የነበረ ግለሰብ ከመንገድ ጠርዝ ጋር በመጋጨት የአሽከርካሪው ህይወት ማለፉን አብራርተዋል፡፡

በክ/ከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ቀን ብቻ በደረሱ አደጋዎች የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉን በመግለጽ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያርጉ እንደሚገባ ኃላፊው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review