AMN – ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጐት ለዜጎች የዘመናት ቁጭት ምላሽ የሚሰጥና ወደ ቀደመው ታሪካዊ ቁመናዋ የሚመልሳት የሕልውና ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
ከቀይ ባሕር በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መገኛ፣ የገናና ታሪክ ባለቤትና ማንነቷ ከባሕር በር ባለቤትነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ናት።
ይሁን እንጂ ከሰላሳ ዓመታት በፊት በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ሆን ብለው በሠሩት ታሪካዊ ስህተት፣ የውጭ አጀንዳን ለማስፈጸም ሲሉ የመግቢያና መውጫ በሮቿን በማስዘጋት ሀገርን የባሕር በር አልባ አድርገዋታል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን የባህር በር ያጣችበት መንገድ ሕጋዊና ታሪካዊ መሠረት የሌለውና ሀገርን ሆን ተብሎ ለማዳከም የተሰራ ሴራ ነበር።
አሁን ላይ የሕልውናዋ ጉዳይ የሆነውን የባህር በር ጥያቄ በመነጋገር፣ በዲፕሎማሲ እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ለማስመለስ እየሠራች ትገኛለች።
የዘርፉ ምሁራንም ኢትዮጵያ በባህር በር ባለቤትነት የምትከተለው የሰጥቶ መቀበል እና የቀጣናዊ ትስስር ዲፕሎማሲ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን በተለያየ ጊዜያት ይመሰክራሉ።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኢትዮጵያ ያጣችውን የባህር በር መልሳ ለማግኘት የምታደርገውን ሁለንተናዊ ጥረት ተረድቶ ድጋፉን እያሳየ መጥቷል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ የማይቀር ጉዳይ ነው፤ ይህም በቀይ ባሕር አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት፣ ቀጣናዊ ትስስርንና የንግድ ደኅንነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የነበራትንና አሁን ላይ በሴራ ፖለቲካ ያጣችውን የባህር በር ማግኘት እንድትችል፣ ዜጎች ልክ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁሉ በተባበረ ክንድና በጋራ ጥረት እውን ሊያደርጉት ይገባል።
በበረከት ጌታቸው