ወንዞቿን በማከም ለነዋሪዎቿ እፎይታን የሰጠችው አዲስ አበባ

You are currently viewing ወንዞቿን በማከም ለነዋሪዎቿ እፎይታን የሰጠችው አዲስ አበባ

AMN – ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ለዘመናት የቆሻሻ ማከማቻ እና የኢንዱስትሪ ፍሳሾች መጣያ ሆነው የቆዩትን ወንዞቿን አክማ በማዳን ለከተማዋ ነዋሪዎች የጤና እፎይታንና አዲስ ተስፋን ሰጥታለች።

ቀደም ሲል ለጤና እና ለዕይታ አደገኛ፣ እንዲሁም ለህገ-ወጥ ተግባራት የተጋለጡ የነበሩት እነዚህ የወንዝ ዳርቻዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተካሄደው የተቀናጀና ከፍተኛ የልማት ርብርብ ዛሬ ላይ ተፈጥሯዊ ማንነታቸውን ተላብሰዋል።

የወንዞቹ ውሃ ታክሞ ንጹህ ከመሆኑም በላይ፣ ጠፍተው የነበሩ ተፈጥሯዊ ምንጮችም እንደገና ማፍለቅ በመጀመራቸው፣ የውሃው ጤናማነት ሙሉ በሙሉ እንዲረጋገጥ ሆኗል።

ይህ ለትውልድ ተሸጋሪ እንዲሆን ታስቦ የተገነባው የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ለነዋሪው ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ መሰረተ-ልማቶችን አካቷል።

ዘመናዊ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌት እና የእግረኛ መንገድ መስመሮች፣ መንፈስን የሚያድሱ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ ለማንበቢያ የሚሆኑ ጸጥታ የሰፈነባቸው ቦታዎች፣ የአካል ብቃት ማዘውተሪያዎች እና ደህንነታቸው የተጠበቀ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎችን ያካተተ ለትውልድ የሚሻገር ሁለንተናዊ ልማት ተከናውኖባቸዋል።

ፕሮጀክቱ የወንዝ ብክለትን ከመከላከል ባለፈ፣ የከተማዋን የጎርፍ ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። በተጨማሪም የተበከለ ውሃን አጣርቶ ጥቅም ላይ በማዋል የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል እና ምንጮችን ለማጎልበትም አስችሏል።

የከተማ አስተዳደሩ “ከተማን ማልማት ሁለንተናዊ ልማት ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ባካሄደው በዚህ ስራ፣ ከተማዋን ውብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ቱሪዝም ተወዳዳሪ ማድረግ ተችሏል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህ የወንዝ ዳርቻዎች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ዋና መዳረሻ፣ የተለያዩ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ኩነቶች ማስተናገጃ፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች ጤናማ እና ጽዱ የአየር ንብረት መገኛ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

አዲስ አበባ ሁሉን አካታች በሆኑ የልማት ስራዎቿ የቆሸሹትን እያጸዳችና እያስዋበች፣ እንደ ስሟ ውብ፣ ማረኪ እና ጽዱ የሆነ ገጽታን ለነዋሪዎቿ ማስረከቧን አጠናክራ እንደምትቀጥል የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review