የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር በመሆን በሰላምና በልማት ወደፊት መጓዝ አለበት- አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

You are currently viewing የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር በመሆን በሰላምና በልማት ወደፊት መጓዝ አለበት- አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም

የትግራይ ሕዝብ ከዚህ በኋላ ያለፉትን ስህተቶች በመተው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በመተባበር ወደ ሰላም፣ ትምህርት እና ሁለገብ ልማት መግባት እንዳለበት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ የትግራይ ሕዝብ እስከ አሁን ከፍተኛ ችግር እና ስቃይ አሳልፏል፤ አሁን ላይ ግን ሁኔታው ያበቃለት በመሆኑ ከእንግዲህ ወደ ኋላ መመለስ እንደማይፈልግና ወደፊት መጓዝ እንደሚሻ ተናግረዋል።

ከትግራይ ውጭ ያሉ የሀገሪቱ ክልሎች በሥራ ጉብኝታቸው በዓይን መመልከታቸውን በማስታወስ፣ ወጣቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተማረ፣ ሰራተኛው በንቃት እየሰራ፣ የልማት እንቅስቃሴዎች በእርሻና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደር በሌለው መልኩ እያደጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተቃራኒው በትግራይ ክልል የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ውድቀት ብቻ መሆኑን የጠቀሱት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ፣ በመሆኑም ሕዝቡና ወጣቱ ለሀገራቸውና ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በንቃት እንዲደራጁ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ መታሰብ አይቻልም፤ እናትንና ልጅን እንደ መለየት ነው ያሉት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ ወጣቱ አካሄዱን በማረም ከኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር አብሮ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ወጣቱ የሰላሙን መንገድ በመከተል ወደ መከላከያ ሠራዊት እንዲገባ ጥሪ ያቀረቡት አረጋዊ በርሄ(ዶ/ር) ፣ ሠራዊቱም ትልቅ ሀገር የመመስረትና የማቀፍ ፍላጎት ስላለው እጁን ዘርግቶ እንደሚቀበላቸው ገልጸዋል።

አሁን ለተፈጠረው የባለአደራ መንግሥትም ሐሳብ በመስጠት፣ ሂደቱን በመከታተልና የራሳቸውን ጥቅም በማስጠበቅ ከዚህ በፊት ሕዝቡን መቀመቅ ከከተተው የህገወጡ ህወሓት የተሳሳተ አሠራር እንዲወጡ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review