AMN- ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ወንጀለኞች ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂን ልትተገብር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በኢንተርፖል የለማው ይሄው ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ስርዓት ሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ሰርተው የተደበቁ ወንጀለኞች ህግን ተከትሎ ለአባል ሀገራት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል ነው።
የፌዴራል ፖሊስ በቀጣናው በገነባው ጠንካራ የወንጀል መከላከል አቅምና ከኢንተርፖል ጋር ባለው የተቀናጀ ትብብር ለአባል ሀገራት የሕግ አስከባሪዎች ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው ስልጠና በመስጠት ከሚታወቀው የኢንተርፖል ግሎባል አካዳሚ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።
የፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በቴክኖሎጂ የታገዙና ውስብስብ የሆኑበት ዘመን ተፈጥሯል ብለዋል።

እነዚህን ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች ለመቆጣጠርና ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡
በዚህም ኢንተርፖል ድንበር ዘለል ወንጀሎችን መከላከልና ወንጀል ሰርተው የተደበቁ አካላት ተላልፈው የሚሰጡበት ዓለም አቀፍ የተጓዦች ትስስር ቴክኖሎጂ ስርዓት ማልማቱን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው በሽብርተኝነት ወይም በሌላ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል የሚፈለጉ አካላትን በየትኛውም ሀገር ላይ በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኞችን ባሉበት ቦታ ለመያዝ ከኢሚግሬሽንና አየር መንገድ ጋር በሚኖረው ቅንጅት ላይ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ወንጀለኛ የትም ቦታ መደበቅ እንዳይችል የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ገቢራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እንዲጠናከር በማድረጋቸው ከኢንተርፖል ጋር ጥብቅ ትብብር መፍጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከኢንተርፖል ጋር በሰራው የተቀናጀ ዘመቻ አንድ ወንጀለኛ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተላልፎ እንዲሰጥና ለህግ እንዲቀርብ ተደርጓል ብለዋል።
ቴክኖሎጂው በቀን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመከታተል ወንጀለኞችን በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በደረቅ ወደብና በሌሎች የትራንስፖርት ዘርፎች የሚስተዋሉ የሽብር እንቅስቃሴዎችና ወንጀሎችን ተከታትሎ መያዝ ያስችላል፤ በቅርቡም ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።