ኢትዮጵያ፦ የዓረቢካ ቡና መገኛና የዓለም ድንቅ የቡና ሥነ-ሥርዓት ባለቤት

You are currently viewing ኢትዮጵያ፦ የዓረቢካ ቡና መገኛና የዓለም ድንቅ የቡና ሥነ-ሥርዓት ባለቤት

AMN – ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን የዓለም አቀፉ የቡና ሀብትና ባህል መነሻ ናት። ቡና ለህዝቦቿ የዕለት ተዕለት ህይወት፣ የትስስር እና የማህበራዊ እሴት መገለጫ በመሆን ፍጹም የተለየና ማራኪ የሆነ አፈላል ሥነ-ሥርዓት ለዓለም ያስተዋወቀች ሀገር በመሆን ትታወቃለች።

በታሪክና በባህል ውስጥ የቡና ስነ ስርዓት የማነቃቂያ ብቻ ሳይሆን፣ የማህበራዊ መስተጋብርና የአብሮነት መድረክ ጭምር ነው። የቡና ሥነ-ሥርዓት ጎረቤት የሚገናኝበት፣ ችግሮች የሚፈቱበት፣ አዳዲስ ወሬዎች የሚበሰሩበት እንዲሁም የወግ እና የወዳጅነት ማሰሪያ ገመድ ሆኖ ለዘመናት ሲያገለግል ቆይቷል።

ይህ ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይሸራረፍ በመሸጋገሩም ዛሬ ላይ የሀገሪቱ ድንቅ የባህል እና ቱሪዝም መስህብ ሆኗል።

የቡና ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት የሚጀምረው ቡናውን በመልቀም፣ በማጠብ እና ምጣድ ላይ በመቁላት ሲሆን፤ ከተቆላ በኋላ የሚወጣው መዓዛ እና የዕጣኑ ጭስ ድባብ የታዳሚውን ቀልብ የሚስብና ልዩ ስሜታዊ እርካታን የሚፈጥር የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው።

ቀጣዩ ሂደት የተቆላውን ቡና በሙቀጫ ወቅጦ በጀበና ማፍላትና ማዘጋጀት ሲሆን፣ ይህም የራሱ የሆነ ጥበብና ልምድ ይጠይቃል። እጣን እየጨሰ፣ ቡና ቁርስ እየተሰጠ እና ቡናው በሲኒዎች እየተቀዳ ለታዳሚው በሚቀርብበት ወቅት የሚከናወነው የማስተናገድ ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያውያንን የእንግዳ ተቀባይነት እሴት በድምቀት ያሳያል።

በተጨማሪም ሂደቱ የመጀመሪያው ዙር አቦል፣ ሁለተኛው ቶና እና ሶስተኛው በረካ እየተባለ የሚቀርብበት ማህበራዊ ትርጉም ያለው ድንቅ እሴት ነው።

ይህ ባህላዊ እሴት ለሀገር ውስጥ ማህበራዊ ትስስር ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ሀገሪቱ ለሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች እና ቱሪስቶች ቀልብ በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አለው።

የኢትዮጵያ ቡና በጀበና ተፈልቶ ሲጠጡ የሚታደሙበት የባህልና የጣዕም ውህደት ለብዙዎች አይረሴ ሀገራዊ ገጽታንና ትዝታን ጥሎ ያልፋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊና ባህላዊ የቡና ሥነ-ሥርዓቷን ከዓለም አቀፍ የቡና ንግድ እና የቱሪዝም ፍላጎት ጋር በማጣመር የሀገርን በጎ ገጽታ ለመገንባት እየተጠቀመችበት ይገኛል።

የቡና አምራችነቷንና የተፈጥሮ ጣዕሟን ከባህላዊ ውበቷ ጋር አዋህዳ ማቅረቧ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተወዳዳሪነት እያጎለበተችው ይገኛል።

ኢትዮጵያ ይህንን ተፈጥሯዊ ስጦታ ወደ ውብ የማህበራዊ ህይወት መስተጋብር በመቀየር ያበረከተችው አስተዋጽዖ ልዩ የሚያደርጋት ሲሆን፣ ይህንን ድንቅ ባህላዊ እሴት ጠብቆ ማቆየትና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በስፋት ማስተዋወቅ የሁሉም ዜጎች ሀገራዊ ኃላፊነት ነው።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review