AMN- ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም
የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ሀገራትን አንድነትና ትብብር በማጠናከር የህዝቦችን ወንድማማችነት ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ሥራ ላይ የዋለው የመደመር እሳቤ በሁሉም መስክ ውጤት እያመጣ ነው።
መደመር ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካም ትልቅ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን የጠቀሱት ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) ፣ በአፍሪካ ደረጃ የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ እሳቤዎችን ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በአፍሪካ አብላጫ ድምጽ አግኝተው የሚመሩ ፓርቲዎች በሚመሰርቱት መንግሥት የህዝቦቻቸውን ህይወት ለመለወጥ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሁለተኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ “ዕድገትን መምራት ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መጻኢ ኢኮኖሚ መሃንዲሶች” በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ በኢትዮጵያ የመደመር እሳቤ ትግበራ የመጡ ለውጦች ቀርቦ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ እየወሰዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ሀገራትን አንድነት፣ ትብብር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ላይ የምትገኝ መሆኑን አንስተው፤ ከ250 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአገራችን መካሄዳቸው ኢትዮጵያ ለሰላም እና ለጉባኤዎች ያላትን ተመራጭነት ያሳያል ብለዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማነቃቃት፣ ለአፍሪካ ሀገራት ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሁም የዲፕሎማሲ ስራዎችን ከማጠናከር አኳያም ጉባኤው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።