በኢትዮጵያ ፓቪሊዮን 63 የውይይት መድረኮች ይካሄዳሉ

AMN ህዳር 1/2019

በ31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) በተከፈተው የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን 63 የተለያዩ የውይይት መድረኮች ይደረጋሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ አይበገሬነት፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና ካርቦን ገበያ ከውይይት አጀንዳዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

ኮፕ 31 ትናንት በቱርኪዬ አንታሊያ ተጀምሯል።

“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን የተከፈተ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ፓቪሊዮኑን በይፋ ከፍተዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር አቶ በረከት ፈሰፃፀዮን ተገኝተዋል።

ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 11 2019 ዓ.ም በሚቆየው የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን 63 የተለያዩ መድረኮች እና ዝግጅቶችን ያስተናግዳል።

መድረኮቹ መንግሥታትን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን፣ ወጣቶችንና የግል ሴክተሩን በአንድ ጥላ ስር በማገናኘት ሰፊ ውይይቶች ይደረጉባቸዋል።

የውይይቶቹ ዋና ትኩረትም ልቀትን መቀነስ፣ የአየር ንብረት አይበገሬነት አቅም ማጠናከር፣ የፋይናንስ አሰባሰብ፣ የኢነርጂ ሽግግር፣ ብዝሀ ህይወት እና የካርቦን ገበያዎች ላይ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የአንታሊያ ተሳትፎ ዋና አላማ የኮፕ 31ን ውጤታማነት በመደገፍ ለአዲስ አበባው ኮፕ 32 ስኬት ጠንካራ መሠረት መጣል መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን እና የአፍሪካን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በማንፀባረቅ፣ መድረኩ የሀሳብ ልውውጥ ለማድረግና አጋርነትን ለማጠናከር ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ዋና ተደራዳሪ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የአየር ንብረት ግቦችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የፋይናንስ አሰባሰብና ኢንቨስትመንት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፓቪሊዮኑ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ለአየር ንብረት አይበገሬነት የሚረዱ አጋርነቶችን ለማጠናከር ያገለግላል ብለዋል።

የብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር አቶ በረከት ፍስሃፅዮን ዋና ተግባራችን የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ቃል ኪዳኖች በብሔራዊ ዕቅዶቻችን ውስጥ በማካተት ወደ ተጨባጭ ውጤት መቀየር ነው ብለዋል።

ፓቪሊዮኑ እነዚህን ዕቅዶች ወደ ዘላቂ የህብረተሰብ ዕድገት ለመለወጥ የሚያስችሉ አጋርነቶች የሚፈጠሩበት መድረክ መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 በአዲስ አበባ ለምታስተናግደው የኮፕ 32 ጉባኤ እንደ አንድ ወሳኝ ምዕራፍ የሚታየው ይህ ፓቪሊዮን፣ የሀገሪቱን የልማትና የአየር ንብረት ተሞክሮዎችን ከማስተዋወቅ ባሻገር የአፍሪካን እና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን ድምጽ ከፍ ለማድረግ ያስችላል።

ቃል ኪዳኖችን ወደ ተግባር በመቀየር ለአፍሪካ እና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚጠቅም ዘላቂ ትብብር መፍጠር ከኮፕ 31 ግቦች መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review