AMN – ኅዳር 5/2019 ዓ.ም
መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ግንኙነትን፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን፣ የኢኮኖሚ እድገትን፣ የጋራ ትርክትን እና ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ያላቸው ሚና የላቀ ነው፡፡
የህዝብ ንቃተ-ህሊናን ከማሳደግ፣ አግባብነት ያላቸውን መረጃዎች ከማሰራጨት፣ በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ ከማገልገል፣ ሰላምና የጋራ ዕሴቶችን ከማጎልበት፣ ፈጠራንና የባህል ልማትን ከመፍጠር እና የሀገር ገጽታን ከመገንባት አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
መገናኛ ብዙሃን እነዚንና መሰል መልካም ሀገራዊ ተልዕኮዎች ቢኖሩትም፣ ዘርፉ በሚፈልገው ባለሞያ፣ በሥነ ምግባር፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ የማይመሩ ከሆነ ግን ሀገርን እና ህዝብን የመጉዳት እድልም አላቸው፡፡
በሞያና በኃላፊነት የማይመሩ የሚዲያ ተቋማት ነጠላና ከፋፋይ ትርክቶችን በማሰራጨት ልማትን ከማደናቀፍ አልፈው ለሰላም መደፍረስ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሚዲያዎች በ”እኛ እና እነሱ” ከፋፋይ ትርክት ሕብረተሰቡን ከመከፋፈል የይልቅ፣ እንደ መደመር ድልድይ ሆነው የጋራ እጣ ፈንታን ያሳያሉ፤ ሃገር የሚያሻግሩ የጋራ ትርክቶችን ይገነባሉ፡፡
በመደመር እይታ ውስጥ ነፃነት ከኃላፊነት ጋር የሚመጣ ሲሆን፣ የሐሳብ ነፃነት ማለት ሌላውን ማጥፊያ ወይም ሀገርን ማተራመሻ ሳይሆን፣ አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ሕዝብን የማንቃት እና ስርዓትን የማሻሻል ኃላፊነት ነው፡፡
የሁሉም መገናኛ ብዙሃን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፣ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በውይይት፣ በመተማመን እና በጋራ ዕይታ እንዲሰለፉ ማድረግ ነው፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችም እንደሚሉት፣ መገናኛ ብዙሃን በህዝብና በመንግስት መካከል ድልድይ ሆነው ከማገልገል እና የመንግስት ፖሊሲዎችን ከማስረጽ ባሻገር ህዝቡ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ መሳተፍ የሚያስችለውን ነጻ የሀሳብ መድረክ መፍጠር እና ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ከንግድ ሩጫ እና ከውድድር መንፈስ ባሻገር፣ ዜጋን የመቅረጽ፣ የሀገርን ህልውና ማስጠበቅ እና ሰላምን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
የጋዜጠኝነት እና የኮሙኒኬሽን ምሁራን በበኩላቸው፣ ሚዲያዎች የመረጃ ነጻነታቸውን ሲጠቀሙ፣ ለሀገራዊ አንድነት እና ለህብረተሰብ ሰላም የሚተርፍ የ”ሰላም ጋዜጠኝነት” አሰራርን መከተል እንደሚኖርባቸው ያስረዳሉ።
ፖለቲከኞችም፣ ሀገር ከሌለ ፖለቲካም እንደማይኖር በመገንዘብ ለሀገራዊ መግባባት በጋራ መቆም እንደሚጠበቅባቸው ያብራራሉ።
የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚገልጹት ከሆነ፣ ሚዲያዎች አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ህዝብን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን፣ ሀገሪቱ ያላትን እምቅ ጸጋ እና አንጡራ ሀብት ወደ ተደራጀ ሀገራዊ ጥቅም ቀይራ ከድህነት እንድትላቀቅ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ እንድትገነባ በቁርጠኝን መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ህዝብን ከሚከፋፍሉ፣ ቅራኔንና ሽኩቻን ከሚፈጥሩ እና ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑ መረጃዎችን ከማሰራጨት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡
ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂና ከድህረ እውነት ዘመን ጋር ተያይዞ የሀገርን ህልውና እና የህዝቦችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ መረጃዎች ሆን ተብለው ስለሚሰራጩ መረጃዎችን በጥንቃቄ መመርመር ይገባል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ ሊሰሩ ይገባል፡፡
በታምራት ቢሻው