AMN ኀዳር 5/2019
ስፖርት የጤናማ ህብረተሰብ ማፍሪያ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማፋጠኛ ብቻ ሳይሆን የሀገር ገፅታ መገንቢያ ታላቅ መሳሪያ ነዉ፡፡
በተለይ የአትሌቲክሱ ዘርፍ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በአለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የተለየ ክብርና ቦታ አለዉ፡፡
በአርካታ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶቹም በእልህ አስጨራጭ ዉድድሮች ዉስጥ አሸንፈዉ የኢትዮጵያን ባንዲራ በአለም አቀፍ መድረኮች ከፍ አድርገዉ አዉለብልበዋል፡፡
አትሌቲክስን ጨምሮ በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች የተገኙት ዉጤቶች የስፖርት መሰረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ ባልተስፋፋበት ሁኔታ መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስፖርት ዘርፍ ያላትን ጸጋ በአግባቡ መጠቀምና ወደ ተደራጀ ሃገራዊ አቅም መቀየር ከቻለች የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ እንደምትችል የተገነዘበዉ የመደመር መንግሥት ለዘርፉ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተገነቡት ዘመናዊ የስፖርት መሰረተ ልማቶችም በዚሁ በመደመር እሳቤ የተገነቡ ናቸዉ፡፡

በርካታ ታዳጊዎች እና ወጣቶችም በየአካባቢያቸዉ በተገነቡ የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች ያላቸዉን ተሰጥኦ ከማሳደግ አልፈዉ ሃገራቸዉን በአለም አቀፍ መድረክ ማስጠራት ጀምረዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ የተገነቡት የተለያዩ የስፖርት ማዘዉተሪያ ሥፍራዎች ወጣቶች አዳዲስ የስፖርት አይነቶችን እንዲለማመዱ ከፍተኛ እድል ፈጥረዋል፡፡
መዲናዋ ከቅርብ አመታት ወዲህ የምታስተናግዳቸዉ አለም አቀፍ የስፖርት ዉድድሮችም ወጣቶች ለዉድድር ራሳቸዉን እንዲያዘጋጁና የመሳተፍ እድል እንዲኖራቸዉ አድርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍጥነት፤ ፈጠራና ጥራትን ማዕከል አድርጎ ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ከሚያደርጋቸዉ ጥረቶች በተጨማሪ የሃገርን ክብር ያስጠሩ አትሌቶችን የሚያስታዉሱና የሚያበረታቱ ተግባራትንም እያከናወነ ይገኛል፡፡
ተተኪ ወጣቶቹ የታላላቅ ስፖርተኞችን ታሪክና ገድል አዉቀዉ ማደጋቸዉ ጠንካራ ሃገራዊ ፍቅር እንዲያጎለብቱ አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡
በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በአትሌቲክስ፤ በእግር ኳስ፤ በብስክሌት፤ በቦክስ እና በሌሎች ስፖርታዊ ዉድድሮች እየታዩ ያሉ ዉጤቶችና መነቃቃቶች ለሃገሪቱ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ ናቸዉ፡፡
ከስፖርት ባህሪ አንጻር ዉጤት የሚገኘዉ መሰረተ ልማት በማስፋፋት ፤ በመንግስትና በባለድርሻ አካላት ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በስፖርተኞችና በስፖርት ባለሙያዎች ተከታታይ ጥረት፤ ህብረትና ቁርጠኝነት በመሆኑ የስፖርት ባለድርሻ አካላት በሁሉም የስፖርት አይነቶች እየተገኙ ያሉትን ዉጤቶችን ለማላቅ በተደመረ አቅም ሊሰሩ ይገባል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ