AMN- ኅዳር 5/2019 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ከቱርኪዬ ጋር ያላትን ዘመናት ያስቆጠረ ታሪካዊ ወዳጅነት በኢንቨስትመንት እና በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ።
31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31) “ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ሀሳብ በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ ነው፡፡
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከቲአርቲ ወርልድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኮፕ 32 ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመሪዎች ደረጃ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ላይ የቆመ መሆኑን አውስተዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ትብብር ማሸጋገር እንደሚገባ ገልጸው፣ የቱርኪዬ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እያደገ ባለው ኢኮኖሚ ውስጥ ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የቱርኪዬ ኩባንያዎች ከፍተኛ ልምድና ብቃት ባላቸው የአገልግሎት፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የኮንስትራክሽን ዘርፎች ላይ በመሰማራት በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ባለው የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ይህ ተሳትፎ በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ላለው የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም ከመሆኑም ባለፈ፣ ለሁለቱም ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል ።
በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ በቱርኪዬ አስተናጋጅነት እና በአውስትራሊያ የድርድር መሪነት እየተካሄደ የሚገኘው የኮፕ 31 ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፏን እንደምትሰጥ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የሁለቱ ሀገራት አጋርነት በሁለትዮሽ ንግድና ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው