ኢትዮጵያ ያከበረቻቸው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ማን ናቸው?

You are currently viewing ኢትዮጵያ ያከበረቻቸው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ማን ናቸው?

AMN-ኅዳር 10/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የገዘፈ ስሟን በስራቸው ከፍ አድርገው ያስጠሩ በርካታ ግለሰቦችን አፍርታለች።

እትብታቸው ለተቀበረበት ምድር በሞያ መስካቸው ከለፉላት መካከል “የኢትዮጵያ እግርኳስ አባት” የሚሰኙት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ይጠቀሳሉ።

ይድነቃቸው ተሰማ ከዘመናቸው ልቀው የተገኙ እና በኢትዮጵያ ከእግርኳ ስም ባለፈ አጠቃላይ ስፖርት መሰረቱን እንዲይዝ ጥረት አድርገዋል።

በእግር ኳሱ ከታዳጊነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በተጫዋችነት ፣ በአሰልጣኝነት ፣ በዳኝነት ፣ በአመራርነት ከዚህም አልፎ በጋዜጠኝነት አገልግለዋል።

ሁለገቡ ባለሞያ እግርኳስን አጥብቀው ቢወዱም ወደ ተጫዋችነት የገቡበት ታሪክ ግን አስገራሚ ነው። በአንድ ወቅት ሶከር ኢትዮጵያ ይህን ፅሁፍ አስፍሮ ነበር።

“ቅዱስ ጊዮርጊስ 1928 ዓ.ም ላይ ተመስርቶ የመጀመሪያውን ጨዋታ አራራት ከተባለው የአርመን ኮሚኒቲ ቡድን ጋር ለማድረግ ቀጠሮ ቢይዝም አንድ ተጫዋች ጎደለበት።

የቡድኑ አባላት በቦታው ያልተገኘውን ጓደኛቸውን ቦታ እንዴት መሸፈን እንዳለባቸው ግራ በተጋቡበት ወቅት በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ (የይድነቃቸው አባት) ግቢ የቄስ ትምህርት ሲማር የሚያውቁት አንድ ታዳጊ በመንገድ ሲያልፍ ያገኙት እና ቆሎ ሊገዙለት ቃል ገብተው እንዲጫወትላቸው ያግባቡታል።

እሱም በሀሳቡ ተስማምቶ በጨዋታው ተሰለፈ ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 ሲያሸንፍም አንድ ጎል አስቆጠረ።

በዚያ ጨዋታ የጀመረው የታዳጊው እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቁርኝትም ለ23 ዓመታት ዘለቀ” ሲል ይድነቃቸው ተሰማ ወደ እግርኳስ ተጫዋችነት የገቡበትን አጋጣሚ አስታውሷል።

ይድነቃቸው ተሰማ በ23 ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታቸው ወሳኝ ተጫዋች ከመሆናቸው ባለፈ ቡድኑን በአምበልነት እና በአሰልጣኝነትም አገልግለዋል።

ከዚህ ባለፈ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1940 ከተቋቋመ በኋላ በ15 ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑን ወክለው ተጫውተዋል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆንም እኤአ 1962 ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የምትዘክረውን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታሸንፍ መርተዋል።

ከመጫወት እና ማሰልጠን ባለፈውም ኳስን በመዳኘት ፣ የኳስ ዳኞችን በማሰልጠን ፣ አንዳንዴም በሬዲዮ ኳስ በማስተላለፍ ፣ የእግር ኳስ ክለቦችና ፌዴሬሽኖችን በማደራጀት ፣ የአሁኑን አዲስ አበባ ስታድየምን ጨምሮ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማስገንባት ፣ ዓለምአቀፍ የስፖርት ጉባኤዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ፣ የስፖርት ህጎች እና ደንቦችን ወደ አማርኛ በመተርጎም ፣ በምክትል ሚኒስትርነት የኢትዮጲያ ስፖርት መሪ በመሆን ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በስኬት በመምራት እንዲሁም በፊፋ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥም በአባልነት ተሳትፈዋል።

ይድነቃቸው ተሰማ ከሀገራቸው አልፈው አፍሪካም የእግርኳሱ በረከት ተቋዳሽ እንድትሆን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በ1949 ካርቱም ላይ በሱዳን ፣ በግብፅ፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ አባልነት ሲመሰረት የተቋሙን መተዳደሪያ ደንብ በመቅረፅ ረገድ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል በመሆንም አገልግለዋል።

ከውጪ ቋንቋዎች እንግሊዘኛ ፣ ፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛ አቀላጥፈው መናገራቸው የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) ለ15 ዓመታት እንዲመሩ እድሉን ሰጥቷቸዋል።

በካፍ ፕሬዘዳንትነት በሰሩባቸው ዓመታት የፈጠሯቸው ለውጦች በብዙዎች አስተሳሰብ እስካሁን ካየናቸው የአፍሪካ እግርኳስ መሪዎች ሁሉ የበለጠ ስኬታማ ያደርጋቸዋል።

በይድነቃቸው የካፍ አመራር ስር በርካታ ፈር ቀዳጅ ስራዎች ተከናውነዋል።

የመጀመሪያው የአፍሪካ የወጣቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ የዋንጫ አሸናፊ ክለቦች ውድድር (የአሁኑ የኮንፌዴሬሽኖች ዋንጫ) በይድነቃቸው ጠንሳሽነት የተጀመሩ ውድድሮች ናቸው።

የካፍ ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግ በ1974ቱ የሊቢያ የአፍሪካ ዋንጫ የቴሌቪዥን እና ስርጭት መብት ታይቶ በማይታወቅ ትርፍ እንዲሸጥ ሚናቸውን ተወጥተዋል።

ይድነቃቸው ተሰማ ከእግር ኳሱ ባለፈ የኢትኦጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲመሰረት እና እርሳቸውም በአመራርነት በማገልገል ይታወቃሉ።

ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲመሰረት እና ጠንካራ ተቋም እንዲሆን ያላቸውን ሞያዊ እውቀት ሁሉ አበርክተዋል።

መስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም ከአባታቸው ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሙላቷ ገብረስላሴ በጅማ ከተማ የተወለዱት ይድነቃቸው ተሰማ በዘርፈ ብዙ ሙያዎች በትጋት ሲያገለግሉ ቆይተው ነሀሴ 13 በ1979 በካንሰር ህመም ምክንያት በ65 ዓመታቸው ህልፈታቸው መሰማቱ በሕይወት ታሪካቸው ላይ ሰፍሯል።

ሀገራቸውን ማማው ላይ ያስቀመጡት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መንግስት ግብራቸውን በሚመጥን መልኩ አስታውሷቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በአደይ አበባ ስታዲየም አቅራቢያ የተሰራላቸው ሀውልት ተመርቋል።

በርካታ የስፖርት ቤተሰብም ሙሉ ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ስፖርት የሰጡት ባለሞያ በመታወሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review