ከተሞች በንጹህ አየር እና በውብ መዓዛ እንጂ በጭስ መታጠን የለባቸውም

You are currently viewing ከተሞች በንጹህ አየር እና በውብ መዓዛ እንጂ በጭስ መታጠን የለባቸውም

AMN ህዳር 12/2019

በኢትዮጵያ ውስጥ በየአመቱ በየአካባቢዉ በጋራ ወጥቶ ቆሻሻን መቃጠል እንደ ዋንኛ የጽዳት መርሃ ግብር ተደርጎ ለዘመናት ሲተገበር ቆይቷል፡፡

አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎችም ታላላቅ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት ቤትና ግቢያቸውን በማጽዳት ለበዓሉ ዝግጅት ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡

ድርጊቱ ቆሻሻን በማቃጠል አካባቢን ማጽዳትና በሽታን መከላከል ይቻላል ከሚል እሳቤ የሚነጭ፤ ሳይንሳዊ፤ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ማረጋገጫ የሌለው ማህበራዊ ልማድ መሆኑንም ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ይህ ልማድ በወቅቱ ከነበረው ማህበረሰብ ግንዛቤ የሚመነጭ ሲሆን፤ ቆሻሻ ስላለው ጠቀሜታም ሆነ ቆሻሻን ማቃጠል ስለሚያስከትለው ጉዳት በቂ ግንዛቤ አልነበረውም፡፡

የጤና እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች እንደሚመክሩት ከሆነ ቆሻሻን አሰባስቦ በግልጽ ቦታ ማቃጠል በሰው ጤና፣ በአካባቢ እና በአየር ንብረት ላይ ከባድና የረዥም ጊዜ ጉዳት ያስከትላል።

ጭሱ በተለይ በከተማ እና በመኖሪያ አካባቢዎች አየርን በፍጥነት ስለሚበክል ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል። በጭስ ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን ብናኞች ወደ ሳንባ ውስጥ በመግባት ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የአስም በሽታ መቀስቀስ እና ብሮንካይተስ ሊስከትሉ ይችላሉ፡፡

ፕላስቲክ፣ ጎማ፣ ቀለም ያላቸው ቁሳቁሶች እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ሲቃጠሉ የተለያዩ ከባድ ብረቶችን ወደ አየር ይለቅቃሉ። እነዚህ ንጥረ ነገሮች የነርቭ ስርዓትን፣ ጉበትን እና የሆርሞን ስርዓትን ሊጎዱ እንዲሁም ለካንሰር ሊያጋልጡ ይችላሉ። ባለሞያዎቹ እንደሚመክሩት ከሆነ የአየር ብክለት የደም ግፊትን እና የልብ ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራል።

ጭስ ዓይንን ያቃጥላል፣ እንባ ያስወጣል፤ እንዲሁም ቆዳን ሊያሳክክ ወይም ሊያስቆጣ ይችላል። ከቃጠሎ የሚቀረው አመድ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን የያዘ በመሆኑ ወደ አፈር ሲሰርጽ የአፈርን ለምነት ይቀንሳል፤ በአፈር ውስጥ የሚገኙ ጠቃሚ ተህዋሲያንን እና እጽዋትን ይጎዳል።

ዝናብ ሲዘንብ የቃጠሎ አመድ እና መርዛማ ቅሪቶች ተጠራርገው ወደ ወንዞች፣ ኩሬዎች እና የከርሰ ምድር ውሃ በመግባት የመጠጥ ውሃን እና የውሃ ውስጥ ህይወትን ይበክላሉ።

በተለይ በደረቅ እና ነፋሻማ ወቅት ቆሻሻ ማቃጠል ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት በማስነሳት በንብረት እና በህይወት ላይ ከባድ አደጋ ያስከትላል።

ለዚህም ይላሉ ባለሞያዎቹ ዘመኑ ከደረሰበት እውቀትና ቴክኖሎጂ አንጻር ቆሻሻን ከማቃጠል ይልቅ በአይነት መለየት፤ ብስባሽ ቆሻሻን ለኮምፖስት መጠቀም፣ እንደገና ጥቅም ላይ ማዋል እና በተፈቀደ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ማስወገድ ይገባል፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት የከተሞችን ንጽህናና ጽዳት እውን ማድረግ የተቻለ ሲሆን ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትም እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ቆሻሻን በየአመቱ በጋራ ወጥቶ በማቃጠል ላይ የተመሰረተው ኋላ ቀር ልማድም የግልና የአካባቢን ንጽህናን በየሰአቱና በየዕለቱ በመጠበቅ ተቀይሯል፡፡

ከተሞች በንጹህ አየር እና ውብ መዓዛ እንጂ በጭስ መታጠን የለባቸውም የሚለውም እሳቤም የዘመናዊነትና የስልጣኔ መገለጫ ሆኗል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review