አዲስ አበባ፣ የመደመር መንግስት ዕይታ ከራዕይ ወደ ተጨባጭ ውጤት የተሸጋገረባት የለውጥ ከተማ!

You are currently viewing አዲስ አበባ፣ የመደመር መንግስት ዕይታ ከራዕይ ወደ ተጨባጭ ውጤት የተሸጋገረባት የለውጥ ከተማ!

AMN -ኅዳር 12/2019 ዓ.ም

የከተማ ልማት የአንድ ወቅት ሥራ ሳይሆን በቀጣይነት የሚገነባ፣ የሚሰፋና የሕዝብን የኑሮ ጥራት በየጊዜው የሚያሻሽል የለውጥ ጉዞ ነው። ዛሬ በአዲስ አበባ እየተመዘገበ ያለው እውነታም ይህንኑ ያረጋግጣል።

የመደመር መንግስት ዕይታ ሰውን ማዕከል ያደረገ፣ የተቀናጀ መሠረተ ልማትን የሚያስቀድም፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያነቃቃና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ከተማን የመገንባት ዓላማ ያለው ነው። ይህ ዕይታም በአዲስ አበባ በተጨባጭ የሚታይ ውጤት እያፈራ ይገኛል።

ከተወሰኑ ኮሪደሮች በተጀመረው የከተማ ለውጥ ጉዞ ዛሬ የበለጠ የተስፋፋ፣ የተቀናጀና ሁለንተናዊ ይዘት ያለው ልማት እየተገነባ ነው። ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ጎላጉል፣ ከእንግሊዝ ኢምባሲ እስከ ሞኤንኮ፣ ከአደይ አበባ ሞዴል መንደር እስከ ሻላ መናፈሻ የተዘረጉት የኮሪደር ልማቶች የዚህ ተራማጅ ለውጥ ጉልህ ማሳያዎች ናቸው።

በ57 ሄክታር ስፋትና 17 ኪሎ ሜትር ርዝመት የተከናወኑት እነዚህ ልማቶች የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን፣ የመሬት ውስጥ መሠረተ ልማቶችን፣ ዘመናዊ የንግድ ሕንፃዎችን፣ የመኖሪያ ሞዴል መንደሮችን፣ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን፣ አረንጓዴ ቦታዎችንና የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማትን በአንድ የተቀናጀ የከተማ ልማት ሥርዓት ያካተቱ ናቸው።

ከዚህም በላይ በግንባታው ወቅት ለ23 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ሲሆን፣ በቀጣይም በንግድ፣ በአገልግሎትና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው። ይህም ልማት የከተማን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ደረጃና የኢኮኖሚ ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን ያሳያል።

አዲስ አበባ ዛሬ በምትገነባቸው መንገዶች፣ ኮሪደሮች፣ አረንጓዴ ስፍራዎችና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የነገዋን ዘመናዊና ስማርት ከተማ መሠረት እያኖረች ነው። የተጀመረው ልማት በየጊዜው እየተስፋፋ፣ የሚፈጥረው ውጤት እየጎለበተና የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት ወደ ከፍታ እያሸጋገረ ይገኛል።

የመደመር መንግስት ዕይታ በተግባር፤ የአዲስ አበባ ለውጥ በተጨባጭ ውጤት! ዛሬን ምቹ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ የጀመርነው የልማት ጉዞ በቁርጠኝነት ይቀጥላል። ከንቲባ ጽህፈት ቤት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review