AMN – ኅዳር 16/2019 ዓ.ም
5ኛው የአፍሪካ ህብረተሰብ ጤና ጉባኤ (CPHIA) ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።
ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ባስተናገደው በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ የገቡ እንግዶች፣ በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።
ከእነዚህም መካከል ወደ 150 የሚጠጉ እንግዶች የዓድዋ ድል መታሰቢያን የጎበኙ ሲሆን፣ በቆይታቸውም ከፍተኛ መደነቅና ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ከናይጄሪያ የመጡት ዶ/ር አሌክሳንደር አንቶን ታሪካዊውን መታሰቢያ በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ የዓድዋ ድል የመላው አፍሪካውያን የጋራ ድልና የኩራት ምንጭ መሆኑን አስታውሰዋል።

በሙዚየሙ ውስጥ የሚገኙ የጦር አዛዦች አልባሳት እና ጥንታዊ የጦር መሣሪያዎች በእጅጉ እንደሳቧቸው የጠቀሱት ዶ/ር አሌክሳንደር፤ አፍሪካውያን የበለጸገ ታሪክ ባለቤቶች መሆናቸውን ለመረዳት ወደዚህ ታሪካዊ ቦታ መምጣት ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተመሳሳይ ከኬንያ የመጣችው ዊኒ ታላም በበኩሏ፣ በመታሰቢያው ውበት፣ ንጽህና እና የታሪክ አቀራረብ ጥልቀት መደነቋን ተናግራለች።
ስፍራው አፍሪካን ከድህነት ጋር ብቻ አያይዞ የመመልከት የተሳሳተ ትርክትን የሚቀይር መሆኑን የገለጸችው ዊኒ፣ የአፍሪካን እውነተኛ ማንነት፣ ሀብትና ታሪክ ከዚህ ቦታ ማየት እንደሚቻል ገልጻለች።
በተለይም በዓድዋ ጦርነት ወቅት ሴቶች የነበራቸውን ታላቅ ሚና የሚያሳየው ክፍል በእጅጉ እንደማረካት የጠቀሰችው ኬንያዊቷ ጎብኚ፣ አፍሪካውያን በአንድነትና በትብብር መቆም እንዳለባቸው መግለጿን ከአድዋ ድል መታሳቢያ የተገኘው መረጀ ያመላክታል፡፡