AMN – ታኅሣሥ 23/2017 ዓ.ም
የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ (East Africa Electric Highway) ፕሮጀክት አካል የሆነው ኃይል ከኬንያ ወደ ታንዛንያ የሚያስተላልፈው መስመር የሙከራ የኃይል አቅርቦት ጀምሯል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት የመጀመሪያው የኃይል ትስስር በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል የተፈጠረ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በተዘረጋው የኃይል አቅርቦት መሰረተ ልማት በኩል የኃይል ትስስሩ እውን መሆኑን የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመረጃው አመልክቷል፡፡
የፕሮጀክቱ ሁለተኛና ከኢትዮጵያ – ኬንያ ፕሮጀክት በመቀጠል በኬኒያና በታንዛንያ መካካል የተዘረጋው የኃይል አቅርቦት ትስስር መስመር ነው፤ ይህ የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተጠናቆ የሙከራ ኃይል አቅርቦት የጀመረው፡፡
ይህ ቀጠናዊ የኃይል ትስስር በተመጣጣኝ ዋጋ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማረጋገጥ በሀገራት መካካል ትብብርን ያመጣል፤ ብለጽግናን ያሰፍናልም ተብሏል፡፡
የኃይል ትስስሩ ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል አቅርቦት በማስፋፋት የአረንጓዴ የኤሌክትሪክ ኃይል ግብይትን በቀጠናው እንዲስፋፋ ሚና እንድትጫወት በማስቻል በመጀመሪያዎቹ የግብይት ዘመናት በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ እንድታገኝ ያደርጋታል።
ለፕሮጀክቱ የአልም ባንክ ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የፈረንሳይ የልማት ፋይናንስ ተቋም ድጋፍ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል።