AMN-የካቲት 28/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በማዕከላዊ ሶማሊያ የታጣቂ ቡድኑ ቁልፍ የጦር ቀጣና በሆነው ሥፍራ አልሸባብን ኢላማ ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሞሐመድ ኑር አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሶማሊያ ፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት በአልሸባብ ጠንካራ ይዞታዎች ላይ በሚሳኤል የታገዘ ጥቃት መፈጸሙን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ በደህንነት ዙሪያ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ትብብር እያደገ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በአልሸባብ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም የዚህ ማሳያ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
እርምጃው ሶማሊያ በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮን እንዲቀላቀል መፍቀዷን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ደህንነት የምታደርገውን የታወቀ ቁጥጥር አመላካች መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ዘመቻውን ለማድረግ የተወሰነውም አልሸባብ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባባበር በቅዱሱ የረመዳን ወር በማዕከላዊ ሸበሌ እና ሂራን በተባሉ አካባቢዎች ከሶማሊያ መከላከያ ኃይል ጋር የሚያካሂደው ውጊያ መባባሱን ተከትሎ እንደሆነም መጠቆማቸውን ጋሮው ኦንላየን ዘግቧል፡፡
በታምራት ቢሻው