AMN- ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም
ጥራት ያለው፣ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና በክህሎት የበለጸገ የሰው ኃይል የማፍራት ተቋማዊ ራዕያችንን የምናሳድግበት ታላቅ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገለጹ፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፣ የአዲስ አበባ ስማርት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አቶ ሚሊዮን በመልዕክታቸውም፣ ቢሮው የከተማዋ ወጣቶች በሙያና በክህሎት የታነጹ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ እና የስራ ፈጠራ ክህሎት ያላቸው አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል ከባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ቢሮው በስሩ ባሉ 14 ነባር የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያና የአገልግሎት ዘርፎች በየዓመቱ በአስር ሺዎች መካከለኛ ባለሙያዎችን እያፈራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ነባሮቹን ከጊዜው ጋር ከማዘመንና ከማሳደግ ባሻገር አዳዲስ ኮሌጆችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ ግንባታው የተጀመረው አዲስ ስማርት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሲጠናቀቅ የማሰልጠን አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግ፣ የሰልጣኞችን ቁጥር የሚጨምር እና የስልጠና ጥራትን ወደ ላቀ ቴክኖሎጂ ደረጃ የሚያሸጋግር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ይህም ቢሮው የያዘውን ጥራት ያለውንና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል የማፍራት ራዕይ በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን ተጨማሪ የትምህርትና የስልጠና ጉልበት ይፈጥርለታል ብለዋል።

ስማርት ኮሌጁ ከ800 በላይ ወጣቶችን በዓመት ተቀብሎ በተለያዩ ዘርፎች ከማሰልጠን በዘለለ በውስጡ በሚቋቋመው የፈጠራ ሥራዎች ማበልፀጊያ ማዕከል (incubation center) አማካኝነት ወጣቶች በስልጠና ወቅት የሚያመጧቸውን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሀሳቦችንና የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባራዊ ቢዝነስ የሚቀይሩበት፣ የራሳቸውን ኢንተርፕራይዞች የሚመሰርቱበትና ለሌሎች ወጣቶችም የስራ እድል የሚፈጥሩበት ማዕከል እንደሚሆን መናገራቻን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡