AMN- ሐምሌ17/2018 ዓ.ም
በናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከኩሪፍቱ ሪዞርቶች/ቦስተን ፓርትነርስ ኃ.የተ.የግ.ማ ጋር በመተባበር በኬንያ የሁለት ቀናት የቱሪዝም ማስተዋወቂያ መድረክ አዘጋጅቷል።
ዝግጅቱ የኢትዮጵያን ልዩ የቱሪዝም እምቅ አቅም ለማሳየትና በአፍሪካውያን መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።
ይህ መድረክ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ለምትጀምረው የቱሪዝም ማስተዋወቂያ ዘመቻ መነሻ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ባጫ ደበሌ፣ ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን ገልጸው፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡ 18 የዓለም ቅርሶችን ጨምሮ ያላትን አስደናቂ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች አጉልተዋል።
በተጨማሪም ለተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ በማደግ ላይ ስላለው የቱሪዝም ዘርፍና ስለ ዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪስት መዳረሻዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ መሪዎች፣ የብዙሃን መገናኛ ተወካዮችና የቅኝት (ቱር) ኦፕሬተሮች ተገኝተዋል።
የዝግጅቱ አካል በሆነው በዚህ መርሐ ግብር ላይ ተሳታፊዎቹ የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህቦች በአካል ተገኝተው ለመጎብኘት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ታውቋል።