የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦው

You are currently viewing የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦው

AMN- ሐምሌ 17/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከሀገራዊ የሥነ-ምህዳር እና የልማት ማዕቀፎች ባለፈ፣ ሀገራችን ዓለም አቀፍ ግዴታዎቿን በብቃት እየተወጣች መሆኑን የሚያሳይ ታሪካዊ እና አርአያነት ያለው ምዕራፍ ነው።

ይህ መርሐ ግብር የተፈጥሮ ምህዋር ከመዛባት በመታደግ ለሰው ልጆች የተሻለች፣ ጤናማ እና ደህንነቷ የተጠበቀች ምድርን ለማስረከብ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ትግል ውስጥ የላቀ ድርሻ አለው።

አሁን ላይ የደን መመናመን፣ የካርቦን ልቀት መጨመር እና የአየር ንብረት መዛባት መላውን የሰው ልጅ ሕልውና እየተፈታተኑ የሚገኙ ዓለም አቀፍ አደጋዎች ናቸው።

በዚህ ወሳኝ ሰዓት ኢትዮጵያ በሰፊው እያከናወነችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የከባቢ አየርን ንጹህ ማድረግ እና የምድርን ሙቀት ለመቀነስ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት በተጨባጭ በመደገፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን መቋቋምን ዓላማ እውን እያደረገ ይገኛል፡፡

ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ የተሻለ ሕይወት እና አስተማማኝ የምግብ እና የአካባቢ ደህንነት ማረጋገጥ ዓላማንም እውን እያደረገ ነው፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን አርቆ አሳቢነት የሚያሳየው ከዓለም አቀፍ ትልልቅ ፖሊሲዎች እና ማዕቀፎች ጋር ባለው ጥልቅ ትስስር ጭምር ነው።

መርሐ ግብሩ በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ላይ ሀገራት የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የገቡትን ቃል በተግባር የሚተረጉም ግዙፍ ሀገራዊ ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር፣ ዓለም አቀፍ ግቦች ጋር በቀጥታ ይጣጣማል፡፡

የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ፣ ጤናማ ሥነ-ምህዳርን ከማስቀጠል፣ ድህነትን ከመቀነስ እና ከአየር ንብረት እርምጃዎች ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው።

የአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳም፣ “የምንፈልጋትን አፍሪካ” እውን ለማድረግ አረንጓዴ እና ብልጽግናን የተላበሰች አህጉርን ለመፍጠር የሚደረግ የመጀመሬያው ጥረት ነው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያን ጽኑ አቋም እና ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ኃላፊነት በግልጽ የሚያሳይ የድል ምዕራፍ ነው።

ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ተነሳሽነት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጽናት ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ዓለም ሰላም፣ ጤና እና የተሻለ የኑሮ መሰረት የሚጥል የዘላቂ ልማት ማዕዘን ድንጋይ ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ ሰፊ የትውልድ አሻራ ዘመቻዋ ለዓለም አርአያ መሆንን ቀጥላለች።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review