የመዲናችን ኪነ ጥበባዊ ድግሶች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች  እና አዳዲስ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይቷል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የስዕል ዓውደ ርዕይ፣ የመጻሕፍት ምረቃ፣ የቴአትር መርሐ ግብር፣ እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል መርሐ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

መጻሕፍት

“ስካርፍ፣ ቡና ና ጢስ” መጽሐፍ በዛሬው ዕለት ይመረቃል፡፡ የገጣሚ አንዱ ጌታቸው “ስካርፍ፣ቡና ና ጢስ” የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8:30 ጀምሮ በመሶብ የሙዚቃ ማዕከል ውስጥ ይመረቃል። “ስካርፍ፣ ቡና ና ጢስ” መጽሐፍ በቅድመ ሽያጭ በ300 የጀርባ ዋጋ ለአንባቢያን ቀርቦ እየተሸጠ መሆኑ ይታወቃል። በዕለቱም የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያን በመድረኩ እንዲገኙ ገጣሚው ጋብዟል፡፡

“ሕይወት እንደ መንገድ” መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ በገጣሚ ጋሻው የኃላሸት (ዘቢደር) የተዘጋጀው “ሕይወት እንደ መንገድ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠው አዲስ መጽሐፍ በቅደመ ክፍያ ሽያጭ ለንባብ ሊበቃ እንደሆነ ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡

ስለመጽሐፉም ገጣሚ ጋሻው የኃላሸት በማህበራዊ ትስስር ገፁ ተከታዩን ብሏል፤ “እነሆ የህትመት ብርሃንን ዘመኑ በዋጀው ዘይቤ ልንቋደስ ‘ሕይወት እንደ መንገድ’ ብለን የቅድመ ክፍያ አማራጭን ተከተልን፡፡ ስለዚህ የሥነ ጽሑፍ ወዳጆች የዚህች መንገድ ምርኩዝ ትሆኑኝ ዘንድ ልባዊ ቀረቤታዬ እነሆ! …እንግዲህ እንደ ውዴታችሁ ይህቺን መድብለ ግጥም በነጠረ ወዳጅነት፣ ሚዛኑን በጠበቀ ውዴታ፣ በፍቅር ስለፍቅር ኑ እናሳትማት!” ሲል የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያንን ጠይቋል፡፡ 

የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል የመጀመሪያ የሥዕል ኤግዚቢሽን ለህዝብ ክፍት ሊሆን ነው፡፡ “ጣይቱ” የተሰኘ ከ24 በላይ ታዋቂ አንጋፋና ወጣት ሰዓሊያን የተሳተፉበት የሥነ ጥበብ ትርኢት በታሪካዊው የአዲስ አበባ የመጀመሪያ ማዘጋጃ ቤት በነበረውና በአሁኑ የጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል ውስጥ ከፊታችን ሰኞ አንስቶ ለህዝብ ክፍት ይሆናል፡፡ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከስዕል በተጨማሪ ልዩና ደረጃቸውን የጠበቁ ኪነ ቅርጾችም ይቀርባሉ ተብሏል። ይህ የሥዕል አውደ ርዕይ ለ15 ቀናት (እስከ ግንቦት 30 ቀን) ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡ ይኽ አጋጣሚ እንደ አዲስ የተጠገነውን ታሪካዊ ቅርስ ቤቱን ለመጎብኘትም ታላቅ ዕድል ጭምር በመሆኑ የንባብ አፍቃሪያን በዝግጅቱ እንዲታደሙ ተጋብዘዋል፡፡ የሥዕል አውደ ርዕዩ የሚታይበት አድራሻ፣ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ከእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጎን ሲሆን፣ የፊታችን ሰኞ 11፡00 ሰዓት አውደ ርዕዩ በይፋ ይከፈታል፡፡

የስዕል አውደ ርዕይ

“የተሸመኑ ትውስታዎች” የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በወጣቱ ሠዓሊ ብርሃኑ ማናዬ የተዘጋጁ ሥዕሎች የቀረቡበት “የተሸመኑ ትውስታዎች” የሥዕል አውደ ርዕይ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ በሚገኘው “The Space Ethiopia” የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ በቅቷል። በዳግም አበበ አጋፋሪነት የተዘጋጀው ይህ አውደ ርዕይ የተለያዩ የስዕል አቀራረቦችን እንዲሁም በተለያዩ የአሳሳል ዘይቤ የተሰሩ የስዕል አይነቶችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል። አውደ ርዕዩ እስከ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በዕይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

በሌላ መረጃ ደግሞ የአይዳ ሙሉነህ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በአይዳ ሙሉነህ ተዘጋጅቶ በ ዘ-ኢንድ ፈንድ አዘጋጅነት እና በሪቺንግ ዘ-ላስት ማይል ድጋፍ ለህዝብ የቀረበው ሪፍሬሚንግ ኔግሌክት የተሰኘ የፎቶ አውደ-ርዕይ በመታየት ላይ ይገኛል። በገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ማዕከል እየታየ ባለው በዚህ ዓውደ-ርዕይ፣ አይዳ ሙሉነህን ጨምሮ የሰባት አፍሪካዊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ስራ ስብስብ ቀርቦ በመታየት ላይ ነው፡፡

በስራዎቻቸው ጠንካራ ታሪክን በፎቶ የማስቀረት እና ማህበረሰቡ የሚያልፍበትን እውነታ የማንፀባረቅ ድንቅ ችሎታ ያላቸው የስድስት አፍሪካዊ ባለሙያዎች 54 የሥነ ጥበብ ስራዎችና ዘጋቢ‐ፎቶዎች የተካተተበት ዓውደ-ርዕይ ሥነ-ጥበብ ምን ያህል ወሳኝ ጉዳዮችን የማጉላት ትልቅ አቅም እንዳለው ያሳያሉ ተብሏል፡፡ አውደ ርዕዩ ባለፈው ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተከፈተ ሲሆን እስከ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ለዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና አሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት  ይገኙበታል፡፡ ባሎች እና ሚስቶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል። 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡እሁድ በ8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን፤ እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር፣ “ጥቁር እንግዳ” ተውኔት ሐሙስ በ12፡00 ሰዓት በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review