AMN- ግንቦት 8/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሀገር ውስጥ አምራችነትን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለመፍጠር በ93 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ የገነባውን ግዙፉን የገላንጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዛሬው እለት በይፋ መርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
በምረቃው ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ግንባር ቀደም ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ2 ሺህ 9 መቶ በላይ ለሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች የመስሪያ ቦታ፣ የብድር እና የመሬት አቅርቦት ችግሮችን የመፍታት ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

በርካታ ሼዶችን በመገንባት ትናንት ጥቃቅንና አነስተኛ የነበሩ ድርጅቶች ወደ ኢንዱስትሪያሊስትነት መሸጋገራቸውንም ገልጸዋል።
የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ 116 አምራች ኢንዱስትሪዎችን በማቀፍ እስከ 20 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ተብራርቷል።
የከተማዋን በጀት ብክነት በሌለበትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል በርካታ የብልጽግና አሻራዎች በተግባር እየተረጋገጡ መምጣታቸውንም ከንቲባዋ ገልፀዋል።

ለአብነትም በፓርኩ አቅራቢያ ወደ 60 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ያሉት አዲስ የመኖሪያ ከተማ እና ለልማት ተነሺዎች መንደር እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም፣ ከተማዋ ከአርሶ አደሮች ጋር በጋራ የመልማት ፖሊሲን በመከተል፣ መሬታቸውን በፈቃደኝነት ለለቀቁ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ቋሚ ገቢ የሚያገኙበት ባለ 14 ሄክታር የግብርና ልህቀት ምርት ማዕከል መገንባቱንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የልማት ተነሺዎቹ በፓርኩ ውስጥ ባሉ ሱቆች የጥሬ እቃ አቅርቦትና የገበያ ትስስር እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ይታረስ የነበረውን ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለልማት ለለቀቁት አርሶ አደሮች ታላቅ ምስጋናና ክብር ያቀረቡ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ለውጥ ማንንም የሚያፈናቅል ሳይሆን፣ የነዋሪዎችን ህይወትና አኗኗር አብሮ የሚያዘምን መሆኑንም በድጋሚ በተግባር አረጋግጠናል ብለዋል።
በሚካኤል ህሩይ