የሩሲያ ዩክሬን ግጭት በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ላይ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ለአንድ ሚሊየን ሰዎች ሞት፣ ከ10 ሚሊየን በላይ መፈናቀል እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት ውድመትን አስከትሏል፡፡
ጦርነቱ ዛሬም ድረስ መቋጫ ያልተበጀለት መሆኑ ሞትና ውድመት ማስከተሉን እንደቀጠለ ነው፡፡
በጦርነቱ ሂደት የምዕራቡ ዓለም ማለትም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የኔቶ አባል ሀገራት ጠቀም ያለ ወታደራዊ፣ የፋይናንስ እና ሰብዓዊ ድጋፎችን ለዩክሬን ያቀረቡ ሲሆን፣ በአንጻሩ በሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ በመጣል ጦርነቱን ከማርገብ ይልቅ አባባሽ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ህንድ፣ ቻይናና ብራዚል ደግሞ ማናቸውንም ሳይደግፉም ሳይነቅፉም የመሀከለኛውን መንገድ የተከተሉ ሀገራት ናቸው፡፡ በዕርግጥ ህንድና ቻይና ከሩሲያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብር ያደርጋሉ፡፡
እንደ ሰሜን ኮሪያ፣ ኢራን እና ቤላሩስ ያሉት ደግሞ ለሩሲያ በሚያደርጉት ወታደራዊና የደህንነት ድጋፍ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትብብር ምክንያት የሩሲያ አጋር ተደርገው የተፈረጁ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና መሠል ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ ጦርነቱን በመኮነን እና የጦር ወንጀል መፈጸሙን በመመርመር ለግጭቱ መፍትሔ የማፈላለግ ሚና ሲወጡ የተስተዋሉ ናቸው፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ተካሮ የቆየውን አለመግባባት እና ግጭት በድርድር ለማስቆም የተደረጉ በርካታ ጥረቶች ቢኖሩም ግን ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም፡፡
ጦርነቱ በተቀሰቀሰ በአራተኛው ቀን ላይ የመጀመሪያው ድርድር በቤላሩስ በሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት መካከል ተደርጎ ያለ ምንም ስምምነት የተለያዩበት ነበር፡፡
ሁለተኛው ዙር ድርድር ደግሞ መጋቢት 2022 ላይ በቤላሩስ እና ዩክሬን ድንብር አቅራቢያ በምትገኝ አንታልያ በተሰኘ የቱርክ ከተማ ተካሂዷል፡፡በወቅቱ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም በዩክሬን በምትገኘው ቡቻ ከተማ ላይ ሩሲያ ያደረሰችው ጥቃት ባስከተለው የበርካታ ዜጎች ህልፈት ምክንያት ስምምነቱ ወዲያው ተቀልብሷል፡፡
መሰል የሰላም ንግግሮች በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን መምጣተቸውን ተከትሎም በአሜሪካ በኩል የስምምነት ሂደቱ እንደ አዲስ ተጀምሯል፡፡
ይሁንና የትራምፕ ቅሬታ የሚያጭር ንግግር የዩክሬንኑ ፕሬዝዳንት የተበሳጩ በመሆኑ የሰላም ንግግሩ በመሪዎቹ መካከል በተፈጠረ የተካረረ ግንኙነት ምክንያት ዛሬም ድረስ እልባት ሳያገኝ ዘልቋል፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን በጦርነቱ ሚሊዮኖችን ከዓይናቸው ቢሰወሩም ዛሬም ድሮን፣ ሚሳኤል እና ሌሎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ከመወራወር አልተቆጠቡም፡፡
በማሬ ቃጦ