AMN – ሰኔ 26/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የአጭር፣ የመካከለኛ ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጀምሯል።
ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ከተለያዩ ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ፌዴሬሽኑ እንደገለጸው፣ ውድድሩ ከ100 ሜትር እስከ 3 ሺህ ሜትር የሩጫ ዓይነቶችን ጨምሮ በሜዳ ተግባራት የሚካሄድ ነው።

ክለቦች በውድድሩ ላይ ታዳጊና ዋና አትሌቶቻቸውን እያሳተፉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኮማንደር አበበ መኮንን ተናግረዋል።
ይህ ውድድር ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም የተመለሰ ሲሆን፣ በስታዲየሙ መካሄዱ የተሻለ ሰዓት ለማስመዝገብ ምቹ መሆኑን ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
ውድድሩ የዓመቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር በመሆኑ፣ አቋማቸውን ለመመዘን ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ተሳታፊ አትሌቶችና አሰልጣኞች ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።
በታምራት አበራ