ተማሪዎች ምን ያህል ለፈተና ተዘጋጅታችኋል?

You are currently viewing ተማሪዎች ምን ያህል ለፈተና ተዘጋጅታችኋል?

ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ፈተና ሲደርስም ሆነ አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ታውቃላችሁ አይደል? መልሳችሁ አዎ! እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ ሊሰጥ ቀናት በቀሩት የ6ኛ ክፍል ከተማ እና ክልል አቀፍ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎችን ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል? ብለን  ጠይቀናቸው የነገሩንን ለሌሎቻችን ጭምር ትምህርት ይሆን ዘንድ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ኢንቲሰር ካሚል እባላለሁ። የምማረው በአበቦች ፍሬ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ፈተናውን በጥሩ ውጤት ለማለፍ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ በትምህርት ቀናቶች ከትምህርት ሰዓት በኋላ አጠናለሁ። በደንብ የማጠናው ግን በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናቶች ነው። በትምህረቴ    ውጤታማ እንድሆን እኔ ከማደርገው ጥረት በተጨማሪ፤ የመምህሮቼ ድጋፍ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በቅዳሜ የማጠናከሪያ ትምህርት የ2016 የሚኒስትሪ ፈተናን ያሠሩናል፡፡ በቤትም ሆነ በትምህርት ቤት ውስጥ ሳጠና የሚከብደኝን ያስረዱኛል፡፡ ቤተሰቦቼም በተወሰነ ደረጃ የሚያስጠኑኝ ሲሆን የሚያስፈልገኝን አጋዥ መጻህፍት ገዝተውልኛል፡፡

 ሌላዋ የአበቦች ፍሬ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ዩስራ ፉአድም በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀች እንደሆነ ነግራናለች፡፡ “በየቀኑ የምማረውን ትምህርት ከስር ከስር አጠናለሁ፡፡ በብዛት የማጠናው ምሽት እና እሁድ ዕለት ነው፡፡ ከ6ኛ ክፍል በተጨማሪ 5ኛ ክፍል የተማርኩትንም እያጠናሁ ነው፡፡ የአጠናን ዘዴዬ አጫጭር ማስታወሻዎችን በማዘጋጀት ነው። የሚከብዱኝን  የሂሳብና እንግሊዝኛ የትምህርት አይነቶችን ትኩረት ሰጥቼ አጠናለሁ፡፡

መምህራን ቅዳሜን እንደ መደበኛ ትምህርት ያስተምሩናል፡፡ በትምህርት ቤቱ የ6ኛ ክፍል የሂሳብ መምህር የሆኑት ንጋቱ መራይ፤ ለተማሪዎቹ ከሚሰጣቸው የማጠናከሪያ ትምህርት በተጨማሪ አባሪ መረጃዎችን እና ያለፉትን ሁለት ዓመት ከተማና ክልል አቀፍ  ፈተናዎችን በተናጠልና በቡድን በብዛት እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፡፡ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ህጻናት እንደመሆናቸው ወደ ጨዋታ ስለሚያዘወትሩ በየእለቱ ጉትጎታ ይፈልጋሉ  ሲሉ እያደረጉት ስላለው ዝግጅት ነግረውናል። 

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት ማርታ ታዬ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ ለ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ከመስከረም ጀምሮ በተከታታይ ቅዳሜ የማጠናከሪያ ትምህርት ሰጥቷቸዋል፡፡ የዘንድሮ ከተማ እና ክልል አቀፍ ፈተና ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ የሚመጣ እንደመሆኑ መጠን በማጠናከሪያ ትምህርቱ የ5ኛ ክፍልን እንዲያስታውሱ ተደርጓል፡፡ ጥያቄዎችን በብዛት ሰርተዋል፡፡ የእንግሊዝኛና ሂሳብ ትምህርቶችን ትኩረት በመስጠት ዕውቀታቸውን የማሳደግ ስራ ተሰርቷል። በትምህርት  ቤቱ  የተዘጋጁትን ጥያቄዎች እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ መልካም የእርስ በእርስ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠርና በሚገባ እንዲዘጋጁ ለማድረግ የጥያቄና መልስ ውድድር ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በስነ ልቦና እንዲዘጋጁም በልዩ ፍላጎት ባለሙያ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡     

ስሜ ደሳለኝ ዱላ እባላለሁ፡፡ የቀይ ኮከብ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ ለሚኒስትሪ ፈተና ዝግጅት እያደረግኩ ነው፡፡ የሚከብደኝን መምህሮቼን እጠይቃለሁ፡፡ መምህራን በትምህርት ቤቱ የተዘጋጀውን ጥያቄ ያሰሩናል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንጫወትበትን ሰዓት ቀንሰው የምንፈተናቸውን የትምህርት አይነቶች ይከልሱልናል፤ ያስጠኑናል፡፡ እቤቴም ታላቅ እህቴ ታስጠናኛለች፡፡ በደንብ እየተዘጋጀሁ ስለሆነም የሞዴል ፈተና አልከበደኝም፡፡

አላዛር አቡ ሌላው የትምህርት ቤቱ ተማሪ ነው፡፡ ማጥናት የጀመርኩት የ5ኛ ክፍል መማሪያ መጽሐፍት ላይ ያሉ መልመጃዎችንና ማጠቃለያዎችን በመሥራት ነው፡፡ በየዕለቱ የምማረውን ትምህርት አነባለሁ፡፡ ባለፈው ዓመት የተፈተኑትን የሚኒስትሪ ፈተናንም እየሠራሁ ነው፡፡ ትምህርት ቤታችንም ለ6ኛ ክፍል ተማሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ ቀን ከሚሰጠን የማጠናከሪያ ትምህርት በተጨማሪ፤ ከሰኞ እስከ አርብ ባለው የትምህርት ጊዜ የእረፍት ሰዓታችንና ወደቤታችን ከመሄዳችን በፊት ያሉ ጊዜያትን ተጠቅመው ያስጠኑናል፡፡ በደንብ እየተዘጋጀሁ ስለሆነ የሚኒስትሪ ፈተናን ጥሩ ውጤት አምጥቼ  እንደማልፍ  እርግጠኛ ነኝ፡፡      

መምህር መሀመድ ታደሰ በትምህት ቤቱ ምክትል ርእሰ መምህር ናቸው። በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለፈተና ዝግጁ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል። ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከጥናት እስከ የፈተና አሰራር (እንዴት ማጥቆር እንዳለባቸው) ድረስ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ በትምህርት ቤቱ ከመደበኛው ትምህርት ሰዓት በተጨማሪ እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ በምሳ ሰዓት ካላቸው የእረፍት ሰዓት 30 ደቂቃ እና ወደ ቤታቸው ከሚወጡበት ከዘጠኝ ሰዓት አስቀድሞ 15 ደቂቃ በመቀነስ ለተማዎቹ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ለፈተና ብቁ የሚሆኑበት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በተሰራው ስራም በሞዴል ፈተና ውጤታቸው የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የተዘጋጀ ተማሪ ደግሞ ፈተናውን በጥሩ ውጤት ያልፋል፡፡ ጥሩ መዘጋጀት ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ ወደ ፈተና ቦታ በሰዓቱ መሄድ፣ የፈተና ጥያቄዎችን በአትኩሮት ማንበብ እና መልሶችን መስጠት ይገባል፡፡ መልካም የጥናት እና የፈተና ጊዜ እንዲሆንላችሁ የዝግጅት ክፍሉ ምኞቱን ይገልፃል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review