መገናኛ ብዙሃን ማህበረሰባዊ ንቃት በመፍጠር ለሀገራዊ የጋራ ጉዳዮች እና ጥቅሞች እንዲተባበር የማድረግ ስራን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ እና ከግል መገናኛ ብዙሃን ከተወጣጡ ባለሞያዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የመጨረሻው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መገናኛ ብዙሃን ለሀገር ግንባታ፣ ለሰላም እና ልማት ቀናኢ የሆነ፣ የኢትዮጵያን የጋራ ራዕይ ለመገንባት የሚተጉ፣ የጸና አቋም ያላቸው፣ ለዘላቂ ጥቅም የሚተጉ እና የጋራ አስተሳሰብን የሚገነቡ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን በሀገራዊ ራዕይ እና ግብ የታቃኙ መሆናቸው ለሀገር ግንባታው ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።
ማህበረሰብን ማንቃት ዋንኛ ተልዕኳቸው እንደሆነም ጠቅሰው የነቃ ማህበረሰብ ብሄራዊ ጥቅሙን በውል የሚገነዘብ እና የሀገሩን እድገት አጥብቆ የሚሻ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ትልሞች አሏት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ጉዳዮችን በውል ተረድተው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የመንግስትን ስኬቶች ብቻ ሳይሆን ድክመቶቹንም ነቅሶ በማውጣት ሚዛናዊ የሆነ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ ያልተሰራች የምትገነባ ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙሃን ሀገር እየሄደችበት ያለውን መንገድ ተከትለው መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።