በአማራ ክልል የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ልማት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ(ዶ/ር) ገለጹ።
የቢሮ ኃላፊው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግስት ሁልጊዜ ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ ይሰጣል።
በክልሉ በጫካ ያሉ የታጠቁ አካላት የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለሰላምና ለልማት እንዲሰሩ ተደጋጋሚ ጥሪ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ወራት በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ መደበኛ ህይወታቸውን መምራት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ለመጡ 12ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና ለመስጠትና ወደ ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ቀደም ብሎ የክልሉ መንግስት በከተሞችና ቀበሌዎች ባካሄደው ህዝባዊ የምክክር መድረክ ህዝቡ ለሰላም አማራጭ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ማረጋገጫ መስጠቱን አንስተዋል።
የሰላም አማራጭን በመግፋት የክልሉን ህዝብ በግጭት እንዲቆይ በሚያደርጉ ታጣቂዎች ላይ መንግስት የሚወስደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ለማገዝ ሕዝቡ በቁርጠኝነት መቆሙንም ተናግረዋል።
የጽንፈኛ ኃይሉ ቀሪ ታጣቂዎችም በግጭት የሚፈታ አንዳች ጥያቄ አለመኖሩን በመገንዘብ መንግስትና ህዝብ የሰጣቸውን የሰላም አማራጭ እንዲጠቀሙበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶ ስልጠና በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በመገባደድ ላይ ባለው በጀት ዓመት ያለፉት ወራትም የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 10ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎች ከስህተታቸው በመማር መደበኛና ሰላማዊ ሕይወት የሚመሩበት ዕድል እንደተፈጠረላቸው ማብራራታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተሳሳተ ስሌት ወደ ግጭት የገቡ የፅንፈኛ ቡድኑ አባላት ከስህተታቸው ትምህርት በመውሰድ መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ እየተቀበሉ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የክልሉ ህዝብ የታጣቂ ቡድኑ አባላት አለን የሚሉትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንዲችሉ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የታጣቂ ኃይሉን የመረጃና የፋይናንስ ምንጭ በመበጣጠስ ህግና ሥርዓት የማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ የጸጥታ መዋቅርና የሠራዊት አባላትም ህብረተሰቡን በማሳተፍ የክልሉን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።