ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወር የምታስመርቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት፣ ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የጀርባ አጥንት መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ፣ በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የውኃ ኢንቨስትመንት ሰሚት ጉባኤ የሚንስትሮች ከፍተኛ የፓናል ውይይት ላይ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመጠናቀቅ ላይ ስለሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ግንባታ ፋይናንስ ስለተደረገበት ሁኔታ ተሞክሮዋን እንድታካፍል ሚኒስትሩ ተጠይቀዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ቀደም ባሉት መንግስታት ዘመን እንዲጀመር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን የበጀት ድጋፍና ብድር ጠይቃ ማግኘት ባለመቻሏ፣ ቀጣዩ ትውልድ እንደሚገነባው በማመን የዛሬውን ትውልድ እንዲጠብቅ መገደዱን አመላክተዋል፡፡
ግድቡ በዋናነት በመንግስት አቅም በሀገር ውስጥ እና ባህር ማዶ በሚገኙ ውድ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ አባላት ቀጥታ ተሳትፎ የተገነባ የአፍሪካ ኩራትና የኃይል ምንጭ ፕሮጀክት መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም፣ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ከ5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ በግንባታ ሥራው የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች በቀጥታ በመሳተፍ አሻራቸውን ያስቀመጡበት ከኃይል ምንጭነት በዘለለ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ዋና ምሰሶ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ ሲጠናቀቅ በዋናነት በግሉ ዘርፍ ላለው ክፍለ ኢኮኖሚ በእጅጉ ትልቅ የኢንቨስትመንት ዕድል ይዞ ይመጣል ያሉት ሚንስትሩ፣ ለዚህ ማሳያው በዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የውኃና ኃይል አቅርቦት የጀርባ አጥንት ሆነው ለሌሎች ግቦች በአማካኝነት የሚያገለግሉ መሆናቸውንም በአጽኖት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኃይል ትሥሥርን በመፍጠር ረገድ በቀዳሚነት ሚናዋን እየተጫወተች መሆንዋን ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ከሱዳን፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ታንዛኒያ ያሉ ሀገራት ጋር የኃይል አቅርቦት እያደረገች ሲሆን፣ ከሌሎች ቀሪ ሀገራት ጋር ደግሞ ስምምነቶች ተደርገው በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማብራሪያውን ተከትሎ በጉባኤው ላይ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ከሚኒስትሩ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ሚኒስቴሩ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል፡፡