የመዲናዋን ነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing የመዲናዋን ነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑ ተገለጸ

AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

የመዲናችንን ነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳችን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ከተማ አቀፍ የጎርፍ መከላከልና የአደጋ ዝግጁነት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ።

መርሐ ግብሩን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደተናገሩት፣ ንቅናቄው በተለይም በክረምት ወራት ደረቅ ቆሻሻዎች ወደ ፍሳሽ ማስወገጃዎች በመግባት ለጎርፍ አደጋና ለሌሎች ችግሮች መንስኤ እንዳይሆኑ መከላከልን ታሳቢ ያደረገ ነው።

ወንዞች የንፁህ ውሃ መውረጃና መዝናኛ እንጂ በዜጎች ላይ አደጋ የሚያደርሱ መሆን እንደሌለባቸው የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ የመዲናችንን ነዋሪዎች ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ አጀንዳችን ነው ብለዋል።

ከተማዋ ያከናወነቻቸው የልማት ስራዎች የከተማዋን ተወዳዳሪነት ያሳደጉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ጃንጥራር፤ አደጋዎችን አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎችም ከልማቱ ጋር መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በቅርብ ጊዜ የጎርፍ አደጋን የመከላከል ስራ ውጤት እየታየበት ቢሆንም፣ አሁንም በከተማዋ ትኩረት የሚሹና ያልጸዱ ሰፈሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

ነዋሪዎችም የአካባቢያቸውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ በመከላከል ከተማቸውን ጽዱ፣ ውብ እና ጤናማ በማድረግ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢ መሆኑን አስታውሰዋል።

አደጋውን የመከላከል ተግባር በክረምት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review