የገጠሩን ማህበረሰብ ኑሮ የመቀየር እና ምርታማነትን የማሳደግ ተግባር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ባጠረ ጊዜ ማሳካት የሚያስችል መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የክረምት ስንዴ ምርት አሰባሰብን ጎብኝተው የበጋ ስንዴ እርሻ ሥራን ማስጀመራቸው ይታወቃል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት የገጠሩን ማህበረሰብ ኑሮ የመቀየር ስራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ባጠረ ጊዜ ማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።
መንግስት ከተሞችን የመቀየር እና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት በርካታ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ መግባቱን አንስተው በኢትዮጵያ አብዛኛው ማህበረሰብ የሚኖረው በገጠር ክፍል መሆኑንና መንግስት በገጠር የሚኖሩ ዜጎችን ኑሮ ለመቀየር እና ምርታማነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በአትክልት፣ ፍራፍሬና ሰብል እጅግ አበረታች ውጤት መገኘቱንና የምስራቅ ሸዋ ዞን የስንዴ ምርት ስራ የሚያመላክተው ይህንኑ ነው ብለዋል።
በዞኑ ያለው የኩታ ገጠም የስንዴ እርሻ በኮምባይነር እየታጨደ መሆኑን በማንሳት ይህም ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ነው አፈ ጉባኤው የገለጹት።

ኢትዮጵያ ስንዴ፣ ሩዝ እና አቮካዶን ጨምሮ በተለያዩ ምርቶች ራሷን ለመቻል እያከናወናቸው ያለው ስራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ስንዴ ከመግዛት ተላቃ በራሷ የማምረት አቅም ማሳደጓ የዚሁ ስራ ማሳያ ነው ብለዋል።
የተጀመረውን ስራ አጠናክሮ በመቀጠል በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጉዞ ማሳካት እንደሚቻል ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በኦሮሚያ ክልል በገጠር ትራንስፎርሜሽን እየተከናወነ ያለው ስራ በሌሎች ክልሎችም እየተከናወነ መሆኑን በመጥቀስም ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል።
የገጠሩን ክፍል ለመቀየር እየተከናወነ ያለው ስራ እጅግ ተስፋ የሚሰጥና አበረታች መሆኑንና ተደራሽነቱን በማስፋት የኢትዮጵያን ብልጽግና በአጠረ ጊዜ እንደሚሳካ አያጠራጥርም ነው ያሉት።